አርዕስተ ዜና

ኅዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች መንግሥት ትክክለኛ መልስ ለመሥጠት ተዘጋጅቷል-አምባሳደር ስዩም መስፍን Featured

06 Jan 2018
387 times

ሪያድ ታህሳስ 28/2010 በኢትዮጵያ ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች መንግሥት ትክክለኛ መልስ ለመሥጠት መዘጋጀቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመካከለኛው ምስራቅ አማካሪ አምባሳደር ስዩም መስፍን ገለጹ።

አምባሳደር ስዩም መስፍን እና በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር በሳዑዲ አረቢያ መዲና ሪያድ ከተማ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

አምባሳደር ስዩም መስፍን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የመንግሥት አመራሩ በወቅቱ  ሊፈታቸው  የሚገባቸው ጉዳዮች ነበሩ።

ይሁንና እነዚህን ችግሮች ከመፍታት ይልቅ በሌሎች ነገሮች በመጠመድ መንግሥት እልባት ሳይሰጣቸው በመቅረቱ ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች መከሰታቸውን አውስተዋል።

እነዚህም ችግሮችን ለመፍታት በኢህአዴግና በእህት ድርጅቶች መካከል የተለያዩ ተከታታይ ሰብሰባዎች ቢካሄዱም የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ያደረገው ጥልቅ ውይይት ከዚህ ቀደም ከነበሩት የሚለዩ ናቸው።አሁን መንግሥት ጥያቄዎቹን ለመመለስ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለጥያቄዎቹ መልስ መስጠት የህልውና ያክል አንገብጋቢ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ በርካታ ቀዳሚ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ከወዲሁ መለየታቸውንም ነው ያስረዱት።

በዚሁ ወቅት የመገናኛ ብዙኃንም የሕዝብን ጥያቄ ከማስተጋባት ይልቅ መንግሥትን ማወደስ ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራታቸው ለችግሮቹ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ይህንንም አሁን ላይ ከሥር መሰረቱ በመለወጥ ሚዲያው ከሕዝቡ ጎን እንደሚቆምና ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። 

በተለይም ከአመለካከት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ምንም እንኳን አመራሩ ቢያቃቸውም ትኩረት ሳይሰጣቸው ያለፋቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል  በአገር የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የዳያስፖራው ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን ጥረቱ ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ገልጸዋል። 

ኢህአዴግ ባለፉት አስራ አምስት ቀናት ባደረገው ስብሰባ በአገሪቱ የሚታዩትን ወቅታዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ግምገማ ማድረጉን  አስታውቀዋል። 

ይህንንም ተከትሎ እራሳቸው በፈጸሙት ወንጀል አልያም ደግሞ አቃቤ ሕግ ክስ በመመስረቱ በሕግ-ጥላ ሥር የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከእስር አንደሚፈቱም አማካሪው አስታውቀዋል።

ይህም የመድብለ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በአገሩቱ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ በመታመኑ መሆኑን ድርጅቱ ያስታወቀ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ የሚታወቀው ማረሚያ ቤት ተዘግቶ በሙዚየምነት እንዲያገለግልም ውሳኔ መተላለፉንም ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ