አርዕስተ ዜና

ኢህአዴግ አሁን የደረሰበትን የሀሳብ አንድነት ተግብሮ ሕዝቡን ለመካስ በትጋት ይሰራል…የብሔራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት Featured

03 Jan 2018
472 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ አሁን የደረሰበትን የሀሳብ አንድነት በተግባር በመግለጽ ሕዝቡን ለመካስ ተግቶ እንደሚሰራ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት አስታወቁ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደውን ግምገማና የደረሰበትን ውጤት አስመልክቶ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሀፈት ቤት ማበራሪያ ሰጥተዋል።

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው “ከሰማይ በታች ምንም ዓይነት ነገር እንዲቀር አልተደረገም” በሚል በገለጸው የ17 ቀናቱ ግምገማ   ከመቼውም ጊዜ በላይ የሀሳብ አንድነት በመፍጠር ባለ ስምንት ነጥብ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባር መሰረት መጣሉ ነው የተገለጸው።

ግምገማውን ገና ከጅምሩ “ታሪካዊ ለማድረግ ታስቦ” የተገባበት በመሆኑ ሁሉም ድርጅቶች በአሸናፊነት የወጡበት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ደረጃ ለተፈጠረው ችግር የአካል ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ግምገማ ማድረጋቸውን ነው ሊቃነ መናብርቱ ይፋ ያደረጉት።

በአገሪቷ ለተፈጠረውና በግልጽ እየታየ ላለው ችግር ሥራ አስፈጻሚው ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ለችግሩ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ የሚያስችለው ቁመና ላይ መገኘቱንም ነው ያረጋገጡት።

በአሁኑ ግምገማ የተፈጠረው አመለካከት ለተግባር አንድነት መነሻ እንደሚሆን ያረጋገጡት ሊቃነ መናብርቱ፤ ሥራ አስፈጻሚው በፍጥነት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት ወደ ተግባር መግባቱን  አረጋግጠዋል።

በግንባሩ ውስጥ እርስ በእርስ መጠራጠርና አለመተማመን እየሰፈነ የመጣበት ሁኔታ እንደነበረ   አስታውሰው  ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ጠለቅ ያለ ግምገማ መደረጉንና የሃሳብ አንድነት መፈጠሩን  ገልፀዋል ።

የኢህአዴግና የደኢሕዴን ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው በነጻነትና ግልጽነት ወስኖ በገባው መሰረት የሀሳብ አንድነት ለመፍጠር ያስቻለውን ጥልቅ ውይይት አድርጓል።

የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና የብአዴን ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን እንደገለጹት ደግሞ፤ ችግሮቹ ያሉት በአንድ ድርጅት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘንድ መሆኑ ታይቷል።

በግምገማው የተፈጠረውን የሀሳብ አንድነት ወደ ተግባር ለመቀየር መወሰኑንም ነው የገለጹት፡፡

የኦህዴድ ሊቀመንበር ለማ መገርሳ በበኩላቸው ግንባሩ ጤናማ የፖለቲካ ሂደቱን ጠብቆ ለመሄድ ችግሮቹን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጡ ወሳኝ  መሆኑን ተናግረዋል።

በግምገማው ሁሉም ነገሮች በቡድንም ሆነ በግል በግልጽ መታየታቸውን አመልክተው፤ አገሪቱን  ጥያቄ ውስጥ የከተተው ሁኔታ በጥልቀት መታየቱንና በግልጽ ውይይት መደረጉን አረጋግጠዋል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንደተናገሩት በአሁኑ ግምገማ ቀደም ብሎ በተካሄዱ ተሃድሶዎች ያልታዩ ጉዳዮችንም መፈተሽ ተችሏል።

በውስጥ የነበሩ ክፍተቶችን፣ መጠራጠሮችንና አለመተማመንን ለመፍታት ያስቻለ  ውይይት  መደረጉንም ነው የጠቆሙት።

በሌላ በኩል ብሄራዊ ድርጅቶቹ ውስጠ ዴሞክራሲ እየጠፋ መምጣቱ ለድርጅቱም ሆነ ለአገሪቷ አደገኛ መሆኑን በመገንዘብ የማስተካከያ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

ይህም  ለቡድንተኝነትና መጠቃቀም በር መክፈቱን ጠቁመው  መርህ አልባ ግንኙነት እንዲሰፍን አድርጎ መቆየቱንም አብራርተዋል ።

በግንባሩ ውስጥ የታየው የውስጠ ዴሞክራሲ እጦት ወደ ሌላ እየተላለፈ የሀሳብ መንሸራሸርን የገታ ሲሆን፤ ጉዳዮች በመርህ ደረጃ አለመታየታቸው  ለችግሮቹ መስፈንና ለመርህ አልባ ግንኙነቱ መፈጠር መንስኤ መሆናቸው ተመልክቷል።

በግንባሩ ውሰጥ “እኔ ትክክል ነኝ“ የሚል አስተሳሰብ እየነገሰ መምጣቱንም ነው ሊቃነ መናብርቱ ያመለከቱት።

በዚህም በግለሰባዊና ቡድናዊ ስሜት ተገፋፍተው  ስህተቶች መፈጠራቸው ተጠቁሟል።

በግንባሩ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ከማድረግ አኳያ የነበሩ ጉድለቶች መታየታቸውንም ጠቁመዋል።

የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ የተቃዋሚ  ፓርቲዎች ተሳትፎ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋትና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲያብብ ከማድረግ አኳያ የነበሩ ተጽዕኖዎች በዝርዝር መፈተሻቸውን ሊቀመንበሩ አብራርተዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ባረጋገጠ መንገድ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ