አርዕስተ ዜና

የዩኒቨርሲቲው ሰላም እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በወላይታ ሶዶ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

03 Jan 2018
338 times

ሶዶ ታህሳስ 25/2010 በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የወላይታ ሶዶ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተናግሩ፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደትን በሰላማዊ መልኩ ለማስቀጠል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ እንደተመለከተው፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡና ሰላማዊ  የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን የአካባቢው ማህበረሰብ ሚና የጎላ ነው።

በሶዶ ከተማ የቄራ መንደር ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉወርቅ አብርሃም እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ሰላሙ ተጠናክሮ በስነምግባር የታነጸ ሃገር ተረካቢ ትውልድ እንዲያፈራ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ ናቸው።

ተማሪዎችን ተገቢ ወዳልሆነ ድርጊት የሚመሩ አፍራሽ ኃይሎችን መታገል የሚጀመረው ከሕብረተሰቡ መሆኑን ገልጸው ፣ ተማሪዎች ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸውን ጉዳዮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመነጋገር መፍታት እንዳባቸው መክረዋል።

በከተማዋ የጎላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተፈሪ ኃይሌ በበኩላቸው፣ " ዩኒቨርሲቲው ወጣት ተማሪዎች በመልካም ስነምግባር የሚታነጹበት እንደመሆኑ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲጠናከር የበኩሌን ድጋፍ አደርጋለሁ"ብለዋል፡፡

"ባለማወቅና በሌሎች ተነሳስተው ወደጥፋት የሚገቡ ተማሪዎች ካሉ በምክር እንዲመለሱ በማድረግ ኃላፊነቴን እወጣለሁ" ሲሉም ገልጸዋል።

በሶዶ ከተማ የዋዱ ቁስቋምማሪያም ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መላከገነት መከተ ሃጎስ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ ሆነው ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማህበረሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሊነሱ የሚችሉ ችግሮች ካሉ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች በውይይት መፍትሄ በማምጣት ሰላምን የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን እርስ በርስ ያለመተማመን በማስቀረት ዜጎች አንዳቸው ከሌላቸው በመደጋገፍና በፍቅር እንዲኖሩ በማድረግ በኩል እንደእምነት አባት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው፣ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት መስራት በመቻሉና ለሚፈጠሩ ክስተቶች አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት በመቻሉ በተቋሙ የዩኒቨርሲቲው ሰላም መጠናከሩን ተናግረዋል።

"በተቋሙ ብቻ በሚደረግ ጥረት ሰላም የሚረጋገጥ አይደለም" ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፣ በሠላምና ጸጥታ ጉዳይ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ  በተቀናጀ መንገድ ለመንቀሳቀስ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሊጎዱ የሚችሉ አዝማሚያዎችን በእንጭጩ እያስወገዱ ለመሄድ የሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የሰላም ፎረም በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራ በበኩላቸው፣ " የሀገሪቱን የልማት ጎዞ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን የሚጥሩ አፍራሽ ኃይሎችንና ተግባራቸውን የአካባቢው ማህበረሰብ መታገል ይኖርበታል"ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የካባቢው የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሕብረተሰብ ተወካዮች፣ የዞኑ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራሮችን ጨምሮ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ