አርዕስተ ዜና

የመከባበርና የአንድነት እሴትን ለማስቀጠል የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያጠናክሩ የኃይማኖት መሪዎች ገለጹ

03 Jan 2018
391 times

አክሱም ታህሳስ24/2010 ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያዊያን የመከባበርና የአንድነት እሴትን ለማስቀጠል የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያጠናክሩ በትግራይ የሚገኙ  የኃይማኖት መሪዎች ገለጹ።

በሀገሪቱ ለረጅም ዘመናት የቆዩትን የሰላም፣አንድነትና አብሮ መኖር ባህልን ማስቀጠል በሚቻልበት ላይ ትናንት በአድዋ ከተማ የምክር መድረክ ተካሄዷል።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉት መካከል የትግራይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል አባ ጥዑም በርሄ እንዳሉት፣ ሰላም ለማስፈንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የኃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሚና አላቸው።

"ግጭትን ለመከላከል ስለመቻቻልና አብሮ መኖር አትኩረን በየተቋማቱ እያስተማርን ነው "ያሉት አባ ጥዑም፣ በቤተሰብ ደረጃ ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሰላምን ለማስጠበቅ ሁሉም ዜጋ ተደጋግፎ መስራት እንዳለበት ጠቁመው በተለይ ምእመናን በየእምነት ተቋሞቻቸው ውስጥ የሰላም እሴት ግንባታና የአብሮነት እሴት ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን በማጠናከር ሰላምን የሚሸረሽሩና ጥላቻን የሚሰበኩ ኃይሎችን ለመከላከል የኃይማኖት መሪዎች ሚና የማይተካ ነው።

በቅርቡ በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠሩ ግጭቶችን በማስቆም ሰላም እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያስታወሱት አባ ጥዑም፣" በወጣቶች ላይ የኃይማኖት ተቋማቱ ተምሳሌትነታችን የሆነውን የመከባበርና ፍቅርን ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ እንሰራለን "ብለዋል።

የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ሃገረ ስብከት ስራ አሰኪያጅ ንብረኢድ ተስፋይ ተወልደ በበኩላቸው፣ የኃይማኖት መሪዎች ለምእመናን በየእየእምነት ስፍራው ስለ ሰላምና አብሮ መኖር እሴቶችን ሊያስተምሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

" እኛ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ፍቅርና አንድነት ተምሳሌት ነን " ያሉት የኃይማኖት መሪው፣ይህንን እሴት ወደ ትውልድ ለማሸጋገር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

"በመልካም ስነ ምግባር የታነጸ፣ሰላም፣አንድነትና መከባበርን የሚያስቀጥል ትውልድ ለመፍጠር የኃይማኖት መሪዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በትጋት መስራት ይገባል "ብለዋል።

የትግራይ ምዕራባዊ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ምክትል ሊቀ መንበር ሼክ አሊ ኢማም ጌታሁን እንዳሉት የኢትዮጵያዊያን የመከባበርና የአንድነት እሴት ለማስቀጠል ከመንግስት ጋር በመተባበር  እየተሰራ ነው።

የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሃይለሚካኤል ስዩም በበኩላቸው የኃይማኖት መሪዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት እያደረጉት ያለውን ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የኃይማኖት መሪዎችና አባቶች  የጀመሩዋቸውን ጥረቶች አሁንም ሳይታክቱ አጠናክሮው ሊቀጥሉበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የምክክር መድረኩን ያዘጋጀው የትግራይ ክልል የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ