አርዕስተ ዜና

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ለዘላቂ ሠላም መስፈን ድጋፍ እንደርጋለን አሉ Featured

02 Jan 2018
467 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2010 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መድረክ በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጋር በመሆን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መድረክ ከተለያዩ በጎ አድራጎት ተቋማት፣ ከፌደራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

 የመድረኩ ኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ነጋሽ ተክሉ፤ “ያለ ሠላም ማንኛውንም ተግባራት ማከናወን ስለማይቻልና ሠላም የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ ተባብረን መሥራት ይኖርብናል” ብለዋል።

 በመሆኑም መድረኩ በተለይ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

 የኢትዮጵያ ሴቶች ኔትወርክ ማኅበር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድኅን በበኩላቸው፤ በዓለም፣ በአህጉር እና በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ግጭቶች ሴቶች ተጠቂ ሲሆኑ እንጂ የመፍትሔ አካል ተደርገው ሲታዩ እምብዛም አይስተዋልም ብለዋል።

 የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ሕሉፍ ወልደሥላሴ ጉባዔው የተቋቋመለትን ዓላማ አንግቦ በተለይ በኃይማኖት ሽፋን የሚመጡትን ፀረ-ሠላም ኃይሎችን ለመመከት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 በቀጣይም ጉባዔው በተለይ እንደ መልካም አስተዳደር፣ በሠላም ጉዳዮችና መሰል አገራዊ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ገለልተኛ በሆነ መልኩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የጀመረውን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

 ከፌደራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሔ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ መለሰ እንዳሉት፤ በክልሎች መካከል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ ዘዴዎችን በማስቀመጥ በመሠራቱ ውጤት ማምጣት ችሏል።

 “እንደ አገር የሚከሰቱ ግጭቶችን የመከላከልና የመፍታት ስትራቴጂው ትኩረት ሲያደርግ የነበረው በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ነበር” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ስትራቴጂው አሁን በከተሞችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተከሰቱት ችግሮች ያላካተተ ነበር።

 ግጭቶች ቢኖሩም ባይኖሩም የሠላም ባህልን እያጠናከሩ መሄድ እንደ አገር ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ሰላም ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።   

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ