አርዕስተ ዜና

ሙስናን ለመከላከል የደርሻችንን እንወጣለን--- በትግራይ የብዙሀን መገናኛና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች

02 Jan 2018
456 times

መቀሌ ታህሳስ 24/2010 የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በትግራይ ክልል የሚገኙ የብዙሀን መገናኛና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተናገሩ።

የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን " የሙስና ወንጀልን በመከላከል በኩል የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚና " በሚል ርዕስ  በውቅሮ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

በስልጠናው የተሳተፉ ከ150 በላይ የተለያዩ ተቋማት ጋዜጠኞችና የክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያዎች እንዳሉት፣ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል የድርሻቸውን ይወጣሉ።

በትግራይ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተሾመ ጣማለው እንዳለው፣ በአሁኑ ወቅት የልማት ፀር ከመሆን ባለፈ የስርዓቱ አደጋ እየሆነ የመጣውን ሙስናን ለመታገል የብዙሀን መገናኛዎች ተገቢ ሽፋን እየሰጡ አይደለም።

ህዝቡ በጸረ ሙስና ላይ የጀመረውን ትግል ለማጠናከር የብዙሀን መገናኛ ተቋማት ሚና ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጾ፣ "የሚዲያ ባለሙያዎችም የህዝቡን ትግል ለማነቃቃት የሚያስችሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን በመስራት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል" ብሏል።

የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ፕሮግራም ኃላፊ ኢንስፔክተር ገብረሚካኤል ኪዳነ በበኩላቸው፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዳይረጋገጥ ከሚያደናቅፉ ዋናዋና ችግሮች መካከል የሙስና ወንጀል ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል።

"ሙስኞችና ከሙሰኞች ጋር የሚያብሩ አካላትን በመከታተል ተጠያቂ አንዲሆኑ ለማድረግ የብዙሀን መገናኛ ተቋማትና በየደረጃው የምንገኝ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ድርሻ የላቀ በመሆኑ በትኩረት ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።

በትግራይ የሚገኙ የሴቶች የልማት ቡድኖች ሙስናን ለመታገል የጀመሯቸውን ትግሎች በማነቃቃት የተጠናከረ ሥራ አንደሚሰሩ የገለጸው ደግሞ የትግራይ ክልል ሴቶች ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወጣት ኃለፎም ኃይለ ነው።

ሴቶች በሙስና ቀዳሚ ተጎጂዎች መሆናቸውን አውቀው በተናጠልና በማህበር ተደራጅተው ትግላቸውን እንዲያጠናክሩ የሚድያ ድጋፎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በውቅሮ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደ ግምገማዊ ስልጠና የተገኙት የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ ገብረዋሀድ በበኩላቸው የፀረ ሙስና ትግሉ ሳይጠናከር የትም መድረስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም ለሀገሪቱ የሕዳሴ ጉዞ እንቅፋት እየሆነ ያለውን የሙስና ወንጀል በመታገል በኩል የሚዲያ ተቋማትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተገንዝበው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ሙሰኞችን የሚያጋልጡ የምርመራ ዘገባዎችን በማቅረብ ግዴታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ50 ሺህ ለሚበልጡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ