አርዕስተ ዜና

ህብረተሰቡ ሀሰተኛ ሰነዶችን እንዲያጋልጥ ጥሪ ቀረበ

02 Jan 2018
452 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/4/2010 ህብረተሰቡ ለመልካም አስተዳደር መጓደልና ብልሹ አሰራር ምንጭ የሆነውን ሀሰተኛ ሰነድ የሚጠቀሙ አካላትን እንዲያጋልጥ የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ 14ኛውን አለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ''ሀሰተኛ ሰነዶችን በማጋለጥ የጸረ-ሙስና ትግሉን ማጠናከር'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ  በአዲስ አበባ በውይይት አክብሯል።

ኮሚሽነሩ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሙስናን መከላከል ካልተቻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን፣ ሰላምና መረጋጋትን፣ የተጠናከረ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትንና ውጤታማ የፋይናንስ አጠቃቀም ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም።

ህብረተሰቡ ለብልሹ አሰራርና ሙስና ምንጭ የሚሆነውን ሀሰተኛ ማስረጃን በማጋለጥ አገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

ለሙስና ተጋላጭ በሆኑት በመሬት አስተዳደር፣ በግብር አስተዳደር፣ በትላልቅ የመንግስት ግዥዎችና በፍትህ ዘርፎች ላይ ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ የሚፈፀም ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነትን ማሳየት ይገባል ብለዋል።

የጸረ-ሙስና ትምህርትን ለማስፋፋትና ሙስናን ቀድሞ ለመከላከል በትምህርት ቤቶችና በየተቋማቱ በሚገኙ የስነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በኩል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በፀረ ሙስና ትግሉ ተሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ ሀብትና ጥቅምን በማሳወቅና ማስመዝገብ እና ሌሎች ሙስናን መከላከል የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ትግሉን በሃላፊነት የማስተባበር ግዴታውን ይወጣል ብለዋል።

ሀሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የማይገባ ጥቅም ማግኘት ሙስና በመሆኑ ዜጎች በአንድ በኩል ራሳቸውን ከሙስና በማራቅ፣ በሌላ በኩል ሙሰኞችን በማጋለጥ ለእውነት መቆም እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የተፈፀሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሀብት ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ሆርዶፋ በበኩላቸው ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተወሳሰበና  እየጨመረ እንደመጣ ተናግረዋል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን፣ መታወቂያዎችን፣ መንጃ ፈቃዶችን በመጠቀም ከፍተኛ የፋይናንስና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየደርሱ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በቅርቡ በተደረገው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የመጠቆምና የማጋለጥ ስራ በአማራ ክልል 4 ሺህ በጥቆማ፣ 532 ራስን በማጋለጥ ሀሰተኛ ማስረጃዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል 6 ሺህ 447 ራስን ማጋለጥ፣ ከ20 ሺህ በላይ ጥቆማዎች እንደደረሱ ተናግረዋል።

ድርጊቱ በአገር ንብረት እና መልካም አስተዳደር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል የአመለካከት ለውጥ መፍጠር፣ ሀሰተኛ ማስረጃዎችን መቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ሀሰተኛ ሰነድ በቀላሉ እንዳይዘጋጅ በትክክለኛው ሰነድ ላይ ልዩ ምልክት ማዘጋጀት ተቋማት የግድ ሊተገብሩት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ አለም አቀፉን የፀረ ሙስና ስምምነት ተቀብላ የፀረ ሙስና ህግ የአገሪቱ አንድ የህግ ሰነድ እንዲሆን በማድረግ ሙስናን ለመከላከል እየሰራች ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ