አርዕስተ ዜና

ለባለበጀት ተቋማት የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር መተግበሪያ መመሪያ ተዘጋጀ

07 Dec 2017
696 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 የፌደራልና የክልል ባለበጀት ተቋማት የፋይናንስ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት አሰራር መተግበሪያ መመሪያ ተዘጋጀ።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መመሪያውን በተመለከተ የፌደራልና የክልል ባለበጀት ተቋማትን ያሳተፈ ውይይት በአዲስ አበባ ዛሬ አካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ሌላአለም ገብረዮሃንስ እንደገለጹት መንግስት በሚመድበው በጀት እና የአፈጻጸም ግልጽነትና ተጠያቂነት የፋይናንስ አሰራር ስርዓት ሊኖር ይገባል።

በዚህም የመንግስት ተቋማትን ውጤታማነት፤ ተጠያቂነት፤ ግልጸኝነትና ቀልጣፋ አሰራርን ለማሳደግ ሚኒስቴሩ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በ1 ሺህ 23 ወረዳዎች የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።

አሰራሩ በወረዳ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ ቢሆንም በፌደራልና ክልል ባለበጀት ተቋማት ባለመተግበሩ የፋይናንስ ግልጸኝነት ችግር ሲከሰት መቆየቱን አንስተዋል።

በወረዳዎች ላይ የታየውን ውጤታማ የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር ስርዓትን በፌደራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ይህም ዜጎች በግብር የከፈሉት ገንዘብ ለምን ዓላማ እንደዋለ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ ከመስጠት በተጨማሪ የመንግስትና የህዝብ ንብረት እንዳይባክን ቁጥጥር ለማድረግ ያግዛል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ተቋማቱ ሰፊ ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸውና አገራዊ ሽፋን ያላቸው የካፒታል ፕሮጀክቶችን ስለሚያስፈጽሙ ግልጽ አሰራርን እንዲከተሉ ታስቦ መሆኑንም አንስተዋል።

ስለሆነም የፈደራልና የክልል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ የሚያስችል መመሪያ ከጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በተዘጋጀው መመሪያ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የፋይናንስ መረጃዎችን የበጀትና ወጪን፤የመሰረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ፤ የመንግስት ግዥ አፈጻጸምና ኦዲት ግኝት መረጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል አሰራሮች የያዘ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ማህበረሰቡ የተያዘለት በጀት ለምን አላማ እንደዋለና ምን ውጤት እንዳስገኘ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቂ መልስ መስጠት ያስችላልም  ብለዋል። 

ሁሉም የፌደራል፤የክልልና ሌሎች ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በመመሪያው ላይ የተነሱ ነጥቦችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መመሪያዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ቁጥጥር የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ድኤታዋ አሰራሩን በማይተገብሩ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።      

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ