አርዕስተ ዜና

በዓሉ ለአንድ የምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ማህበረሰብ ግንባታ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል- ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ Featured

07 Dec 2017
701 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ አንድ የጋራ ምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ግንባታ ሂደት አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ ነገ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

"የበርካታ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ሐይማኖቶች መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ብዝኃነት በአግባቡ ሳይስተናገድ መቅረቱ ለሕዝቦች ውስጣዊ ትስስር መላላት ምክንያት ነበር" ብለዋል።

ዜጎች ከ23 ዓመታት በፊት በጋራ ባጸደቁት ሕገ መንግሥት ግን ላለመተማመንና ላለመግባባት ምንጭ የነበሩ ታሪካዊ ግንኙነቶች በሂደት እየታረሙና መፍትሔ እያገኙ መጥተዋል ነው ያሉት።

ከ12 ዓመት በፊት ጀምሮ በየዓመቱ የሚከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዜጎች ይበልጥ እንዲተዋወቁና እንዲከባበሩ ከማስቻሉ ባሻገር አንድ የምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የራሱ አውንታዊ ፋይዳ መጫወቱን ነው የተናገሩት።

ቀኑን ስናከብር የተጀመረውን የልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በማስቀጠል ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን ቃል የምንገባበት ዕለት ነው ብለዋል።

ሕገ መንግስቱ አገሪቱ ከነበረችበት የጉስቁልና ታሪክ በመለወጥ ደህንነቷ የተረጋገጠ፣ በፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ የምትገኝና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላት አገር እንድትሆን ማስቻሉንም ተናግረዋል።

በአገሪቱ የተረጋገጠው ሰላምና ደህንነት በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዘንድ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።

ሕገ መንግሥቱ ሳይሸራረፍ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ሁሉም ዜጎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ሕገ መንግስቱን በሚመለከት ወጥ በሆነ መልኩ የግንዛቤ ማስፋት ስራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በነገው ዕለት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሠላምና የአብሮነት በዓል እንዲሆን ርዕሰ ብሔሩ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ