አርዕስተ ዜና

በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመታደግ መረጃ እየተሰበሰበ ነው Featured

07 Dec 2017
665 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት ሳምንታት በውጭ ጉዳይ ግንኙነት፣ በደህንነት ጉዳዮች እና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለመሄድ ሊቢያን የሚያቋርጡ አፍሪካውያን በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ለባሪያ ንግድ ገበያ እየቀረቡ መሆኑን ሲኤን ኤን  ከሳምንታት በፊት በሰራው የምርመራ ዘገባ ማሳወቁ ይታወሳል።

ሚኒስቴሩ በሳምንታዊ መግለጫው እንዳስታወቀው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ያሉበትን ቦታ ማጣራቱን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም እንዳሉት ሊቢያ ውስጥ በአፍሪካውያን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የ21ኛው ክፍለ ዘመን የባሪያ ንግድ ኢትዮጵያ በጽኑ ታወግዛለች። 

ኢትዮጵያ ሊቢያ ውስጥ ኤምባሲ ባይኖራትም ግብጽ ካይሮ በሚገኘው ኤምባሲ አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ያሉበት ቦታ መለየቱን ተናግረዋል።

 ቃል አቀባዩ ዜጎች ሊቢያ ውስጥ ያሉበትን ቦታ መለየቱን ቢገልጹም ለዜጎች ደህንነት ሲባል ቦታዎችን መግለጽ አስፈላጊ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

 የሰዎችን ማንነትና ብዛት በተመለከተም በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ሊቢያ የገቡ በመሆናቸው "ምን ያህል ናቸው፣ እነማን ናቸው የሚለውን  ገጽታን አይቶ መለየት ያዳግታል" ብለዋል።

 ቀጣዩ ስራ ከተለያዩ ድርጅቶችና አገሮች ጋር በመሆን ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር እንደሚሆን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። 

በሊቢያ የአገሪቱ መንግስት ያለው ተጽእኖ ውስን መሆን ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ እንደ ልብ ተዘዋውሮ መረጃ ለመሰብሰብ አዳጋች እንዳደረገውም አንስተዋል።

 ኮትዲቯር ላይ በተደረገው የአፍሪካና አውሮፓ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሊቢያ መንግስት ጉዳዩን ለማስቆም እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ውሳኔ መተላለፉንም አስታውሰዋል።

 እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ይህን የማያደርግ ከሆነ አገሮች የተናጠልና የጋራ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳሉ በዚህም ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም አላት።

 በተመሳሳይ ሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በተመለከተ የአገሪቱ መንግስት ቀደም ሲል የሰጠውን የእፎይታ ጊዜ እንዲራዘም የኢትዮጵያ መንግስት ካንዴም ሁለት ጊዜ እንዲራዘም ቢጠይቅም ዜጎች ሙሉ ለሙሉ አልወጡም።

 በመሆኑም የሳውዲ መንግስት ከህዳር 6 ቀን 2010 ጀምሮ በኃይል መመለስ ጀምሯል ያሉት አቶ መለስ መንግስት ባደረገው ጥረት እስከ ህዳር 26 ቀን 2010 ድረስ 10 ሺህ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ ወስደው በግላቸው ወደ አገር ቤት እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

 በአሁኑ ወቅት በአማካኝ ከ100 እስከ 300 ዜጎች በቀን የጉዞ ሰነድ እየወሰዱ ሲሆን በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን ለመመለስ ጥረቱን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

 የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰቦችና መገናኛ ብዙኃን ዜጎችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ ጠይቋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ