አርዕስተ ዜና

ተሿሚ አምባሳደሮች በአገራቸውና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ Featured

14 Nov 2017
830 times

አዲስ አበባ ህዳር 5/2010 ኢትዮጵያ የምታከናወናቸውን የልማት ሥራዎች ለመደገፍና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውንም ለማጠናከር እንደሚሠሩ በኢትዮጵ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለጹ።

አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሠላምና መረጋጋትን ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት በመደገፍ ከአገሪቷ ጎን እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ዛሬ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የአስር አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀብለዋል። 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚካኤል አርተር እንዳሉት፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን በአፍሪካ ቀንድና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ስትሰራ ቆይታለች።

በቀጣይ ጊዜያትም ግንኙነቱን በማጠናከር በተለይም በኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብትና የፖለቲካ ሂደት የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ጎን ለጎንም የአሜሪካ ባለ ኃቶብቶች  በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በአምባሳደርነት የሥራ ዘመናቸው የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።   

 

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው  በሥራ ዘመናቸው በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በቀዳሚነትም የኢትዮጵያን የልማት ሥራ እንደሚደግፉ ገልጸው የጀርመን ባለኃብቶችና የንግድ ማኅበረሰቦች በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ እንደሚሰሩ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት የሚካሄዱ የፖለቲካና ምጣኔ ኃብት ማሻሻያዎችን በመደገፍ አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት፣ በጤናና በትምህርት ጉዳዮች ለውጥ እያመጣች መምጣቷንና አገራቸውም እንደ ምሳሌ እንደምታወሳት የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የኡጋንዳ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ሬቤቻ አሙግ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በመንግሥታቱ ድርጅት የምታከናውናቸውን ተግባራት ሀገራቸው እንደምትደግፈውም ነው የገለጹት።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት  ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩና በተለይም እ.ኤ.አ በ2063 "የምንሻትን አፍሪካ ለመፍጠር በጋራ እንሰራለን" ነው ያሉት።   

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ጆን ቦርግስታም ደግሞ ከፕሬዝዳንቱ ጋር የነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ ከኅብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን ግንኙነት ለማጠናከርና በተለይም ኢትዮጵያና ኅብረቱ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸውን አጋርነት እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ በዛሬው ዕለት የጆርዳን፣ የኩባ፣ የስዊዲን፣ የማዳጋስካር፣ የስዊዘርላንድንና የአየርላንድን አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤም ተቀብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ