አርዕስተ ዜና

ኢሕአዴግና አራት ተደራዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ አዋጁ ማሻሻያ ላይ ተደራደሩ Featured

14 Nov 2017
815 times

አዲስ አበባ ህዳር 5/2010 ኢሕአዴግና አራት አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ አዋጅ ዝርዝር ማሻሽያ አንቀፆች ላይ ተደራደሩ።

የ11ዱ ተዳራዳሪ ፓርቲዎች ጥምረት 'ምርጫ ቦርድ' የሚለው ስያሜ ወደ 'ምርጫ ኮሚሽን' እስካልተቀየረ ድረስ ምንም ሐሳብ ባለመስጠት  በታዛቢነት ድርድሩን ተከታትለዋል።

ኢሕአዴግ፣ ኢራፓ፣ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ፣ መኢብንና መኢዴፓ ምርጫ ቦርድ የሚለውን ስያሜ ለማስለወጥ የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት እስካላቀረቡ ድረስ 11ዱ ፓርቲዎች ያነሱትን ሐሳብ አልተቀበሉም።

በመሆኑም በዛሬ ውሎ በምርጫ ቦርድ አዋጅ ዝርዝር ማሻሽያ አንቀፆች ላይ ከኢሕአዴግ ጋር የመደራደሪያ ሐሳብ አቅርበዋል።

ኢሕአዴግና አራት አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርዱ አዋጅ 532/99 ከ1 እስከ 61 ያሉት አንቀፆች ላይ የተደራደሩ ሲሆኑ፤ በነገው ውሏቸው ደግሞ ከ62 እስከ 111 ባሉት አንቀፆች ላይ ለመደራደር ዕቅድ ይዘዋል።

አራቱ ተደራራዳሪ ፓርቲዎች በዋናነት በምርጫ አዋጁ አንቀጾች ላይ መሻሻልና መጨመር አለበት ያሉትን የድርድር ሐሳብ አቅርበዋል።

ፓርቲዎቹ ከቦርዱ ዋና ጽህፈት ቤት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉትን ጽህፈት ቤቶች ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች የሚመረጡበትን አሰራር መዘርጋት ፤ ቦርዱ ከድጎማ ወደ ቋሚ በጀት መምጣት፤ የምርጫ ሂደቱ ከሰነድ ወደ ኤሌክትሮኒክስ መሸጋገር አለበት የሚሉ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል።

የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቶች ከሐይማኖት ፣ ከትምህርት ፣ ከሆስፒታሎችና ሌሎች መሰል ተቋማት በምርጫ አንቀጾች ላይ ያለው ርቀት እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው አንቀፆች መሻሻል አለባቸው የሚሉ ሐሳቦችም በፓርቲዎቹ ቀርበዋል።

የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና ሠራተኞች ከዚህ በፊት ገለልተኛ፤ የክልሉ ሰዎችን አወዳድሮ ይቀይርበት የነበረውን አሁን በተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠው ተጠያቂነታቸው ለቦርዱ እንዲሆኑና እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺህ ባይበልጥ የሚለው ከ1 ሺህ 500 አይብለጥ በሚል እንዲተካም ሐሳብ ቀርቧል።

በተጨማሪ እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ገለልተኛ የሆኑና በሕዝብ የሚመረጡ ከአምስት ያልበለጡ የሕዝብ ተታዛቢዎች የሚለውን ከሦስት እስከ አምስት በሚለው መተካት እንዳለበትም ነው ፓርቲዎቹ የመደራደሪያ ሐሳብ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በበኩሉ፤ የቦርዱ በጀት ቋሚ መሆን፣ በትምህርት ወቅት ከትምህርት ቤቶች የምርጫ ቅስቀሳ 500 ሜትር መራቅ አለበት፤ የእምነትና ሌሎች ተቋማት አካባቢ የማይፈቀድ መሆኑን፣ የዋና ይሁን የክልል ቅርንጫፎች ነፃና ገለልተኛ በሆኑ ሰዎች እንዲመረጡ አሰራቧ በግልጽ ማስቀመጡን አንስቷል።

የምርጫ ሥነ-ሥርዓት በኤሌክትሮኒክስ ሊካሄድ ይገባል የሚለውን ሐሳብ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አኳያ፤ ከመሰረተ ልማት ዕድገትና አቅርቦት አንጻር ማገናዘብና ማየት ይገባል ሲልም ምላሽ ሰጥቷል።

በአጠቃላይ በገዥው ፓርቲ አዋጁን ተፈፃሚ ከማድረግ ክፍተት ይኖራል፤ በተመሳሳይ በተፎካካሪም ፓርቲዎች ሕግና ሥርዓት ያለማክበር ችግሮች ይታያሉ የሚሉ ሐቦች ቀርበዋል።

ሁሉም ለፖለቲካዊ ሥነ-ምህዳሩ መስፋትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ ተገልጿል።

የ11ዱ አገር አቀፍ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ ይዘትና የሥራ ድርሻ ላይ ከመደራደር በፊት የምርጫ ቦርድ 'በምርጫ ኮሚሽን' ስያሜ መተካት አለበት በማለት የፀና አቋሙን አንጸባርቋል። 

ኢሕአዴግ በበኩሉ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ስያሜ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ስነ-ምህዳር ጥበትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዕድገት አኳያ ስያሜውን ሊያስቀይር የሚችል ምክንያት ይቅረብና እንወያይበት፤ ካልሆነ አንቀይርም የሚል አቋም ይዟል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ