አርዕስተ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኳታር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ Featured

14 Nov 2017
654 times

ኳታር ህዳር 5/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኳታር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያዩ።

በኳታር ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያኑ ባነሷቸው ጥያቄዎችና በአገር ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኦሮሚያና ሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ ስለነበረው ግጭት፣ ግጭቱ ከፌደራሊዝም ጋር ስላለው ግንኙነት፣ አገር ለማተራመስ በውጭ ኃይሎች እየተከናወነ ያለው ተግባርና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ነዋሪዎቹ ማብራሪያ ከጠየቁባቸው ጉዳዮች ጥቂቶቹ ናቸው።

በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት የሁለቱ ብሄር ተወላጆች ያመጡት ወይም በሁለቱ ክልሎች መካከል ሲደረግ ከነበረው አስተዳደራዊ የወሰን ማካለል ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ግጭቱ በጫት ንግድ ላይ የተሰማሩና ያለአግባብ መክበር የፈለጉ ጥቂት ኃይሎች ተግባር መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት።

በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች መካከል ምንም አይነት ቁርሾ አለመኖሩንም ገልጸዋል።

መንግስት በጉዳዩ ላይ ገብቶ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኪራይ ሰብሳቢነትን በቁጥጥር ስር እስካላዋልን ድረስ ሌላም ችግር ሊመጣ ይችላል" ነው ያሉት።

አገሪቱ እየተከተለች የምትገኘው የፌዴራሊዝም ስርዓት ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው፤ ይልቁንም ፌዴራሊዝም አገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

"ፌዴራሊዝም የግጭት መነሻ ነው ተብሎ ከተወሰደ ስህተት ነው" ብለዋል። 

በየክልሉ የተቋቋሙ ልዩ ኃይሎች መከላከያ በማይደርስባቸው አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ሲባል የተቋቋሙ መሆኑን ገልጸው የግጭቱ አካል ተደርጎ የሚወሰደው ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል።

በየክልሉ የሚገኙ ልዩ ኃይሎች ሰላም በማስከበር ረገድ ጥሩ ስራዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በልዩ ኃይሎች ላይ እየተደረገ ያለውን ዘመቻ በአገር ውስጥም ሆነ በሌሎች ሰላም የማስከበር ተልዕኮዎች መልካም ስም ያለውን መከላከያ ሰራዊት ስም ለማጥፋት ከሚደረገው ጥረት ጋር ተመሳሳይ ነው ብለውታል።

በኳታር የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እውቅና አለማግኘቱ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈትና የባህል ልውውጦችን ለማድረግ ችግር እንደፈጠረበት የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከኳታሩ አሚር ጋር በሚኖራቸው ውይይት ጉዳዩን አንስተው እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን በኳታር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ትንሽ ቢሆንም በአገሪቱ ልማት በተለይም በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነው ይኸው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኳታር ዶሃ የገቡት ትናንት ነው።

በይፋዊ ጉብኝታቸው ከኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታሃኒ ጋር የሁለቱን አገሮች ግንኙነት አስመልከተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

የኳታሩ አሚር ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ