አርዕስተ ዜና

የለውጥ ሰራዊት ግንባታን የማይተገብሩ ተቋማት ሊጠየቁ ይገባል

13 Nov 2017
880 times

አዲስ አበባ ህዳር 4/2010 የለውጥ ሰራዊት ግንባታን የማይተገብሩ ተቋማት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

 የምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።

 እንደ ቋሚ ኮሚቴው ገለጻ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢለዩም በተግባር ውጤት ሲያመጡ ግን አልታዩም።

 የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማዘንጊያ አያቶ "የለውጥ ሰራዊት በመገንባት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመለየትና ኪራይ ሰብሳቢነትን የመታገል ጅምሮች ቢኖሩም የህብረተሰቡን ፍላጎት ማርካት አልቻሉም" ነው ያሉት።

 በመሆኑም የለውጥ ሰራዊት በመገንባት የተለዩ ችግሮችን በተግባር መፍታት በማይችሉ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

 ተቋማት የለውጥ ሰራዊት ግንባታ መርሆዎች፣ አሰራሮችና መመሪያዎችን እንዲተገብሩ ሚኒስቴሩ ኃላፊነት ወስዶ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

 ህብረተሰቡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሁንም ቅሬታ እያነሳ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

 በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከጅምር ያለፈና በተጨባጭ የመጣ ለውጥ እንደሌለ በመጠቆም።

 የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስትር ታገሰ ጫፎ የተሰጠው ማሳሰቢያ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ የተቋማትን የለውጥ ሰራዊት ግንባታ ደረጃ በመከታተል ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

 በተወሰኑ ተቋማት ጠንካራ የለውጥ ሰራዊት ተገንብቶ ችግሮች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚፈቱ ተብለው ተለይተው እየተፈቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

 ሚኒስቴሩ ክትትል የሚያደርግ የሰው ኃይል ችግር እንዳይገጥመው በዝውውር፣ በደረጃ እድገትና በቅጥር እያሟላ መሆኑንም ተናግረዋል።

 ይህን በማይተገብሩ ተቋማት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

 ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት፣ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና የስራ አመራር ኢንስቲትዩትን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት ገምግሞ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ