አርዕስተ ዜና

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ማህበራዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል

12 Oct 2017
619 times

አዲስ አበባ  ጥቅምት 2/2010  የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ባለፉት 25 ዓመታት  ለክልሉ ህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ተግባራት መከናወኑን የድርጅቱ አመራርና አባላት ገለጹ።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች አመራሮችና አባላት ድርጅቱ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት በዓል ከእህት ድርጅቶች ጋር ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

  የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዮናስ ዮሴፍ እንደገለጹት፤ በ25 ዓመታት ውስጥ በክልሉ የጤና ተቋማት ግንባታ ተደራሽ በመደረጉ የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ሽፋን ማሳደግ ተችሏል።

 በክልሉ ከዞን እስከ ቀበሌ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሰማራት የተሳለጠ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ተችሏል ብለዋል።

 በከተሞች የሚኖሩ ህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና የልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የከተማ ልማት ፖሊሲ በመቅረጽ ተግባራዊ መደረጉን አበረታች ውጤት መገኘቱን ነው አቶ ዮናስ የገለጹት።

 ጠባብነት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ምግባርብልሹ አሰራር፣ ሙስናና ሌሎች የልማት ማነቆዎችን በመታገል ህዝቡ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ስራ "የድርጅቱ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ነው" ብለዋል።

 አምባሳደር ሌላአለም ገብረዮሐንስ በበኩላቸው፤ በትምህርት ዘርፍ  ህብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

 በክልሉ ብዙ ቋንቋዎች በመኖራቸው ህብረተሰቡ በራሱ ቋንቋ የትምህርት ስርአት ተቀርፆለት እንዲማር መደረጉን አስታውሰው፤ ይህም እንደ "ትልቅ ስኬት መሆኑን"  አምባሳደሯ ተናግረዋል።

 በክልሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ማደጉንና ይህም የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት ጉልህ ሚና መጫወቱን አክለዋል።

 በቀጣይም የተከናወኑ ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠልና  የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

 በተለይም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱትን አርብቶ አደሮች በአንድ ቦታ በማስፈር የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኙና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ መሰራቱን ተጠቁሟል።

 አርብቶ አደሮቹን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በመቀየር  ከእንስሳት እርባታ በተጨማሪ የግብርና ምርቶችን አምርተው ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ መደረጉንም ነው ተብራርቷል።

 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) መስከረም 29 ቀን 1985 ዓ.ም መመስረቱ ይታወቃል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ