አርዕስተ ዜና

ጠቅላይ አቃቢ ህግ ስለ ሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም የሚሰጠውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ያጠናክራል Featured

12 Oct 2017
658 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 በሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ዙሪያ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚያጠናክር የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገለፀ።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች 10ኛውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ አክብረዋል።

ስለ ሰንደቅ ዓላማ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥና የህግ ጥሰትን መቆጣጠር እንዲሁም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት ኃላፊነትና ተግባር የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ኃላፊነትና ተግባር ነው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማዕረጉ አሰፋ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ የሚሰጡ ግንዛቤዎች መዳበር አለባቸው ብለዋል።

"በቂ ግንዛቤ ባልተሰጠበት ሁኔታ የሚከሰቱ ችግሮችን በደፈናው ወደ ህግ መውሰዱ አዋጭ አይደለም" ያሉት ኃላፊው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሰንደቅ ዓላማን በትክክል በመጠቀም ረገድ የሚስተዋሉ ስህተቶችን ሁሉም አካል በተጠያቂነት ሊያስቆማቸው ይገባል ብለዋል።

የአቃቤ ህግና የህግ ጥናት ማስረፅ አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸው ወርቁ በበኩላቸው በጊዜ ብዛት ያረጁ ሰንደቅ ዓላማዎችን መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነና በህግ ተጠያቂ አንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሰንደቅ ዓላማን ከምሽቱ 12:00 ሠዓት በኋላ አለማውረድና ተጨማሪ ምልክቶችን ጨምሮ መጠቀም በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

"ሰንደቅ ዓላማ የአገራት የሕዝቦች መታወቂያ ካርድ ወይም ምልክት ብቻ አይደለም" ያሉት አቶ እንዳልካቸው ህብረተሰቡ የማንነቱ መገለጫ መሠረት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ህገ-መንግስቱ በሚደነግገው መሰረት በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞችም በተመሳሳይ የሰንደቅ ዓላማን ቀን አክብረዋል።

የፌዴራል ስርዓቱ ለሴቶች እኩልነትና ለህጻናት መብት ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንና በዓሉም የአገሪቱን ሠላም፣ ልማትና የዜጎች መብት መከበር ቀጣይነት የሚረጋገጥበት እንደሆነ በሚኒስቴሩ የህጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ተናግረዋል።

በመሆኑም በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ለህብረተሰቡ የሚሰጠው ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሮ አበበች ተበጀ በበኩላቸው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰንደቅ ዓላማ የሚገባውን ክብር በመስጠት አገሪቱ የጀመረችውን ልማት የማስቀጠል ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ