አርዕስተ ዜና

ምክር ቤቱ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጆችን መርምሮ ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ Featured

12 Oct 2017
553 times

አዲስ አበባ ጥቅምት  2/2010 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጆች ላይ በመወያየት ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ።

 ምክር ቤቱ ዛሬ የሶስተኛ ዓመት የስራ ዘመኑን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ አካሂዷል።

 የቤተሰብ ሕግን ለማሻሻል፣ የከተማ ፕላን፣ የኢንዱስትሪ ኬሚካልና አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርን እንደገና ለማቋቋም፣ የማሪታይም አሰሪና ሰራተኛ ኮንቬንሽን ረቂቅ የማሻሻያ አዋጆች ምክር ቤቱ ዛሬ ከተወያየባቸው መካከል ናቸው።

 የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ አገራት ዓለም አቀፍ ቲንክ ታንክ መመስረቻ ባለብዙ ወገን ስምምነት፣ የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ስምምነትና የፌዴራል መንግስት ሰራተኞችን በተመለከተ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችም እንዲሁ።

ምክር ቤቱ እነዚህን ረቂቅ የማሻሻያ አዋጆች መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷቸዋል።

 የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በኢትዮጵያ ባህል፣ በተወለዱበት አካባቢ ወግ ልማድና ማህበረሰባዊ እሴት ታንጸው እንዲያድጉ በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ፣ በአደራ ቤተሰብና በመልሶ ማቀላቀልና ማዋሐድ ብቻ እንዲያድጉ ማድረግ የፖሊሲው ዋና ዓላማ ነው።

 በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህጻናት የሚደገፉበት ሁኔታና የወላጅ ፍቅር እዲያገኙ ማድረግ በረቂቁ የተካተተ ሲሆን የውጭ አገር ጉዲፈቻ የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።

 የውጭ አገር ጉዲፈቻን በሚመለከት የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የያዛቸው አንቀጾች ተሰርዘው እንዲሻሻል ተደርጓል።

 በፍርድ ቤት የተጀመሩ የውጭ አገር የጉዲፈቻ ጉዳዮች አዲሱ አዋጅ እስኪጸድቅ ድረስ በነባሩ አዋጅ 213/1992 መሰረት ውሳኔ እንደሚያገኙም ተገልጿል።

 የአገሪቱን የእድገት አቅጣጫ መሰረት ያደረገ የከተማ ፕላን ህግ በማዘጋጀት የከተሞችና የገጠር የልማት ማዕከላትን ዕድገት በፕላን መምራት አስፈላጊ በመሆኑ የከተማ ፕላን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀት ማስፈለጉ ተገልጿል።

 የከተማ ፕላን ረቂቅን ለማሻሻል ምክር ቤቱ ያቀረበው ማሳያ አዋጅ ቁጥር 574/2000 በአፈጻጻም ረገድ የታዩበትን ክፍተቶች ለማስተካከል፣ ተጨማሪ አሰራሮችን ለማከልና የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳካት አዳዲስ ፕላኖች በማስፈለጋቸው ነው።

 የህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ባለቤትነት አጉልቶ ለማሳየትና የፕላን ጥሰትን በህግ ተጠያቂ ማድረግም እንዲሁ።

 ሌላው ለምክር ቤቱ የቀረበው ተጨማሪ ረቂቅ አዋጅ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ምዝገባና አስተዳደርን ለመደንገግ የተዘጋጀው ነው።

 የአዋጁ ዓላማ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የሚያስችል አገራዊ ስርዓት በመዘርጋት የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት፣ ከማከማቸት፣ ከማምረትና ከመጠቀም ሂደት ጋር በተያያዘ በሰውና በእንስሳት ጤናና በአካባቢ ላይ የሚያስከትሉ ጉዳቶችን መከላከል ነው።

 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ማቋቋሚያ ቻርተርን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅም ማህበሩ አሁን ካለው አገራዊና ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ጋር ተጣጣሞ እንዲሄድና ራሱን ለመቻል የሚያደርገው ጥረት ተሳክቶ በራሱ አቅም አደጋ ለደረሰበትና ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረስ የሚችልበት ደረጃ ማድረስ በማስፈለጉ መሆኑ ተጠቅሷል።

 የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99ን ለመተካት የተዘጋጀ ሲሆን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ፍልስፍና የሚጠይቀውን ብቃት፣ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስና ስነ ምግባር የተላበሰ ፐብሊክ ሰርቪስ እንዲፈጠር ማስቻል ነው።

 ማሻሻያው አዋጅ ቁጥር 515/99 በስራ ላይ ከዋለ በኋላ በትግበራ የታዩ ችግሮችን ለመፍታትና በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የመልካም አስተዳደር ችግር በመቅረፍ የለውጥ መሳሪያዎችን በብቃት ማስተናገድ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።

 የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም በሰው ሀብት ስራ አመራር ረገድ ያመጣቸውን ውጤቶች ለማጎልበትና ለማስቀጠል፣ ሰራተኞችን ወጥነት ባለው መልኩ ለመምራት፣ እውቀትና ችሎታቸውን በተገቢ መልኩ ለመጠቀም መሆኑ ተነግሯል።

 ማሻሻያው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሏቸውን ሰራተኞች በማቆየትና አዳዲሶችን በመሳብ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ምቹ የስራ ሁኔታዎችን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው የተገለጸው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ