አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ ያለንን ትብብር እናጠናክራለን---የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር Featured

12 Oct 2017
259 times

ባህር ዳር ጥቅምት 2/2010 የኢትዮጵያን የሰው ኃይል ልማት ለመደገፍ ያላቸውን የትብብር ግንኙነት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር አስታወቁ፡፡

የጆንኤፍ ኬነዲ 100ኛ ዓመት የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ፕሬዝዳንቱ በህይወት ዘመናቸው  ያከናወኗቸውን ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ ትናንት ማምሻውን በባህርዳር አባ መንገሻ ገነሜ  ቤተመጸሐፍት  ተከፍቷል።

አምባሳደር ማይክል ሬይነር  በዚሁ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት የጆንኤፍ ኬነዲ " አገሬ ለእኔ ምን ሰራች ብለህ አትጠይቅ፤ ይልቁንስ እኔ ለአገሬ ምን ሰራሁ ብለህ አስብ ባሉት ሀሳብ ይታወቃሉ"  ብለዋል።

የጆንኤፍ ኬነዲ በህይወት ዘመናቸው ለሰብአዊ መብቶች መከበርና ለአሜሪካ ዜጎች እኩልነት ያለሰለሰ ትግል አድርገው ስኬት ያስመዘገቡና መስዋዕት የከፈሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋርም በነበራቸው ጠንካራ ወዳጅነት በትምህርትና ስልጠና፣ በማህበረሰብ ኑሮ መሻሻልና በሌሎች ዘርፎች በትብብር መስራታቸው አሁን ላለው ጠንካራ ግንኙነት መሰረት ጥሏል።

" ባለፉት አስር ቀናት በኢትዮጵያ  ቆይታዬ እንደተገነዘብኩት ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ጉዞ ላይ ያለች ፣ለብልጽግና ትልቅ አቅም የሚሆናት የበርካታ ወጣቶች አገር መሆኗን ነው " ብለዋል አምባሳደር ማይክል ሬይነር ፡፡

የሀገሪቱን የሰው ኃይል ልማት  ለመደገፍ ያላቸውን የትብብር ግንኙነት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ባይሌ ዳምጤ በበኩላቸው ጆን ኤፍ ኬነዲ የነጮች የበላይነት በነገሰበት በዚያን  ዘመን የጥቁሮችንና የሴቶችን እኩል መብት ለማረጋገጥ  ያደረጉትን ጥረት አስታውሰዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ባላቸው ፍቅር አጼ ኃይለ ስላሴን ጋብዘው ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉ ጠቁመው  ከጆን ኤፍ ኬነዲ  የምንማረው የማይቻለውንና ለመድረስ አዳጋች የሆነውን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት  እንደሚቻል ነው" ብለዋል፡፡

የጆን ኤፍ ኬነዲን ሌጋሲ ለማስቀጠል የአሜሪካ መንግስት   ወጣት ተማሪዎች ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን ከሌሎች አገራት ህዝቦች ጋር የሚለዋወጡበት የሰላም ጓድና የአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ አይዲ) መመስረቱም ተመልክቷል።

አውደ ርዕዩን ከጎበኙት መካከል የስምንተኛ ክፍል ተማሪዋ ቤተልሄም አድማሱ የገነሜ ላይብረሪ በአሜሪካኖች ተገንብቶ መጻህፍትና ሌሎች ቁሳቁሶች የተሟሉለት በመሆኑ ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት  ለማግኘት እንደምትጠቀምበት ተናግራለች።

ጆንኤፍ ኬነዲ ከአስተዳደጋቸው  ጀምሮ በትምህርት ቆይታቸውና በኋላም በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች ከአውደ ርዕዩ መገንዘቧንና ትልቅ ትምህርት እንደሚሆንም ገልጻለች።

በባህርዳር ዩንቨርሲቲ ዋናው ግቢ ፕሬዝዳንቱ በህይወት ዘመናቸው የነበራቸውን ስኬትና ተሞክሮ የሚቃኝ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ