አርዕስተ ዜና

የመንግስት የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ

12 Oct 2017
284 times

ድሬደዋ ጥቅምት2/2010 የሀገሪቱን የሕዳሴ ጉዞ ለማሳካት መንግስት የነደፋቸው የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በየደረጃው የሚገኙ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በፌደሬሽንና በህዝብ ተወካዮች ምክርቤቶች የጋራ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ያቀረቡትን የ2010 ዓ.ም የመንግስት አቅጣጫ የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት ዕድገትና የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

በተለይ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማጽናት መንግስት የጀመራቸውን ተግባራት ለማጠናከር ያስቀመጠው አቅጣጫ የሀገሪቱን ዕድገት ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደአስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ለማስጀመር እንዲሁም በድሬዳዋና ሌሎች አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ ለማስገባት አቅጣጫ መቀመጡ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የተጀመረውን ጥረት ያጎለብታል፡፡

አቶ ኤልያስ ደለለኝ የተባሉ የድሬዳዋ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት " ገዢው ፓርታ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ለማጠናከር የጀመረው ውይይት አስደሳች ነው፤ የምርጫ ህጉን ለማሻሻል መወሰኑም የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ያጠናክረዋል " ብለዋል፡፡

መንግስት የወጣቱን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመደበው ተንቀሳቃሽ ፈንድ አበረታች ለውጥ እያመጣ በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ለእዚህም የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሀገርን የሚለውጡ ፕሮጀክቶች በአግባቡ ቢተገበሩ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ የገለፀው ደግሞ ወጣት ማቲያስ እንዳለ ነው፡፡

“በአሁኑ ጊዜ ለሴቶች የተሰጠው ትኩረት ያስደስታል፤ በመሆኑም መንግስት የሚያስቀምጣቸውን ውጥኖች ለማሳካትና ሴቶችን ለመደገፍ  የድርሻዬን  እወጣለሁ”  ያለችው  ደግሞ ወይዘሪት ሰላም አበበ ናት፡፡

አቶ መሀመድ ጠሃ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ተፈጥሮ የነበረውን ጊዜያዊ ግጭትን በማራገብ ሠላምን ለማደፍረስ የተደረገው ፀረ-ሠላም እንቅስቃሴ ዳግም እንዳይከሰት መንግስት አፋጣኝ እርምጃ ቀድሞ መውሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ሰላም ለልማቱ ዋስትና በመሆኑ የብሔር ብሔረሰቦችን ሠላም፣ ፍቅርና አንድነት ለማናጋት ሲሯሯጡ የነበሩ አካላትን መንግስት በአፋጣኝ ለህግ ማቅረብ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ አቶ ስንታየሁ እንግዳው የተባሉ የድሬደዋ ነዋሪ ናቸው።

መንግስት የጀመራቸውን የልማት፣ የሠላምና የዕድገት ጉዞ ለማሳካት በተሰማሩበት መስክ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ