አርዕስተ ዜና

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሰንደቅ ዓላማ የአንድነታችን መገለጫ ዓርማ በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል

12 Oct 2017
380 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 ሰንደቅ ዓላማ የአንድነታችን መገለጫ ዓርማ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣቶችና ሴቶች ገለጹ።

ሰንደቅ ዓላማ የዜጎችን እና የሃይማኖቶች ዕኩልነትን በማስከበር ያስገኘውን ጥቅምና ፋይዳውን በመገንዘብ ሁሉም ሊያከብረውና ሊጠብቀው እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይዘሮ ስንቅነሽ ታደሰ፣ ራህመት ይመርና ወጣት አዲስ አበራ በሰንደቅ ዓላማ ላይ ያላቸውን ስሜት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የማንነት መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የሀይማኖት  ነጻነትና እኩልነት የሚንፀባረቅበት እንደሆነ ተናግረዋል።

አያት ቅድመ አያቶች ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ሕይወታቸውን እንደከፈሉ ሁሉ ወጣቱም የማንነቱ መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት በአስተያየታቸው ጠቅሰዋል።

ሰንደቅ ዓላማው የአገሪቱን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት የዘለቀ አንድነትና ጥንካሬ የሚያሳይ እንደሆነና የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መከበሩ ዜጎች ለሰንደቅ ዓላማ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር እንዲገልጹ ዕድል የፈጠር ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ስለ ሰንደቅ ዓላማ ክብርና ምንነት በማስተማር ግንዛቤውን ማዳበር ያስፈልጋል ተናግረው፤ የሀገራችንና የማንነታችን መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማችንን በትጋት እንጠብቃለን ሲሉም ነው አስተያየት የሰጡት።

10ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም "ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ግብ ተነስተናል" በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ