አርዕስተ ዜና

የውጭ ዲፕሎማሲው ለውጥ እንዲያመጣ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም Featured

12 Sep 2017
586 times

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 በተለያዩ አገሮች የተመደቡ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳሰቡ። 

የአመራር አባላቱን የክህሎት፣ የእውቀትና የአመለካከት ችግሮችን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትን መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር አባላትና ከሚሲዮን መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2009 በጀት ዓመት አፈጻጸም የሥራ ግምገማና የ2010 ዕቅድ ላይ መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በወቅቱ እንደገለጹት፤ አገሪቷ አሁን ካለችበት የእድገት ደረጃ አኳያ በዲፕሎማሲው ዘርፉ የተፈለገውን ያህል ውጤት አልመጣም።

በተለይ በተቋማት ግንባታ፣ በሰው ሀብት ልማት ስምሪት፣ ክህሎት ያለውን አመራር ከመገንባት አኳያ መከናወን የሚገባቸው በርካታ ተግባራት እንዳሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም በሰው ኃይል በኩል ያሉ የአመለካከት ችግሮችን በመፍታት ሁሉም የአመራር አባል በተመደበበት ቦታ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት መረባረብ እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው፤ በቀጣይ የሰው ኃይል የክህሎትና የእውቀት ውስንነትን ለመፍታት ከፍተኛ ተቋማትና የምርምር መሥሪያ ቤቶችን ለመጠቀም አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።  

"ከውጭ ዲፕሎማሲው በዋናነት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል" ብለዋል።

የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ስኬት በዲፕሎማቶች ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል በተለይ ባለሀብቱ፣ ነጋዴው፣ ምሁራን፣ አርቲስቱ፣ ስፖርተኛውና ሎሎችም ዜጎች ግዴታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳቡም ረገድ አምባሳደሮቹ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2009 በጀት ስራ አፈጻጸም ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜን 4 ቀን ድረስ በአዲስ አበባ እና ሐዋሳ ከተማዎች ገምግሟል።

በግምገማው አመራር አባላቱ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት የተለወጡ፣ የተደራጁና በአንድነት የሚንቀሳቀሱ የአገሪቷን የውጭ ፖሊሲ የሚያስከብሩ ተግባራትን በማከናወን ደረጃ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ ታይቷል። 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ