አርዕስተ ዜና

አፍሪካ ሳይንሳዊና አስተማማኝ የሆነ የውሃና የሚትዮሮሎጂ ስርዓት መዘርጋት አለባት ተባለ Featured

12 Sep 2017
669 times

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባትን ጉዳት ለመቆጣጠር ሳይንሳዊና አስተማማኝ የሆነ የውሃና ሚትዮሮሎጂ መረጃ ስርዓት እንደሚያስፈልጋት የአፍሪካ ህብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽን ገለፁ።

በሚትዮሮሎጂ ላይ ያተኮረው የአፍሪካ ሚኒስትሮች ጉባዔ ( አምኮሜት) የውሃና ሚትዮሮሎጂ አገልግሎት ፎረም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

የህብረቱን የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነርን ወክለው በጉባኤው የተገኙት ሚስተር ሁሴን ያምቢ እንዳሉት፤ እኤአ ከ1970 ጀምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ አንድ ሺህ የሚደርሱ ጉዳቶች ተመዝግበዋል።

ከእነዚህም መካከል ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉት ጉዳቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ እንደተመዘገቡ አስታውሰዋል።

ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በአማካይ ከአስራ አንዱ ስምንቱ በአየር ንብረት ለውጥ በሚከሰት ችግር ምክንያት በድህነት ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት የኮሚሽነሩ ተወካይ፤ ጉዳቱ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የከፋ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በ2016 በኢትዮጵያ ብቻ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ መጎዳታቸውንም ለአብነት አንስተዋል።

በመሆኑም አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስን ጉዳት አስቀድማ ለመከላከል በውሃና ሚትዮሮሎጂ አገልግሎት አማካኝነት  "አስተማማኝ የውሃና የአየር ንብረት መረጃ ስርዓት መዘርጋት አለባት" ነው ያሉት።

በአህጉሪቷ እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥርና የከተሞች መስፋፋት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

በፎረሙ ላይ የተገኙት የውሃ መስኖና ኤለትሪክ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤  በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት ጉዳት አፍሪካ እያስመዘገበችው ያለውን የኢኮኖሚ እድገት እየተፈታተነው ይገኛል።

የአፍሪካ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስን ጉዳት በተቀናጀ መልኩ ለመቆጣጠር መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ሚንስትሩ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅዷ ላይ ለአየር ንብረት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልፀው፤ በአገሪቷ እየተተገበረ ያለውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በአገሪቷ የተቀናጀና ዘመናዊ የውሃና ሜትሪዮሎጂ መረጃ ስርዓት ለመገንባት በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በፎረሙ ከታደሙ 615 ተሳታፊዎች መካከል ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተወከሉ 35 ሚንስትሮች ይገኙበታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ