አርዕስተ ዜና

የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዎች እንዲጠናከሩ የበኩላችንን እንወጣለን....የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ አካላት

12 Sep 2017
625 times

ደብረ ብርሃን መስከረም 2/2010 በሀገሪቱ የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዎች ተጠናከረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የጸጥታ አካላት ገለጹ።   

በደብረ ብርሀን ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዞኑ ፀጥታ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱ ወረዳዎች የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት ተጠናቋል።

ከምክር ቤቱ ተሳታፊዎች መካከል የአሳግርት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ንጉስ ተስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት አሥር ዓመታት በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሥራዎች በመከናወናቸው በዘርፈ ብዙ እድገቶች ተመዝግበዋል።

እነዚህ እድገቶችና ለውጦች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

ኢንስፔክተር ንጉስ አንዳሉት፣ በወረዳቸው በየዓመቱ እስከ 16 የሚደርሱ በቂም በቀል፣ በመሬት ይገባኛል፣ በስካርና በመሳሰሉት ምክንያቶች ይከሰቱ የነበሩ የነፍስ ግድያ ወንጀሎችን የግጭት አስወጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሮ በመሰራቱ እንዲቆም ማድረግ የተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ እንስፔክተር ምንውየለት ጭንቅሎ በበኩላቸው በ2009 በጀት ዓመት ከማህበረሰቡ ጋር በተደረሰ የጋራ ስምምነት ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል በኩል አመርቂ ሥራዎች ተሰርተዋል።

በዞኑ የተመዘገበው ሰላምና መረጋጋት የኢንቨስትመንት ፍሰቱና የንግድ እንቅስቃሴው እየተስፋፋ እንዲመጣ በማድረጉ በተያዘው ዓመት ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በብቃት አንደሚወጡ  አስታውቀዋል።

የዞኑ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድአፍራሽ አባተ በበኩላቸው እንደገለጹት በዞኑ 439 ቀበሌዎች የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጸጥታ ኃይሉ እንቅስቃሴ ላይ ማህበረሰቡ ያበረከተው አስተዋጽኦ በዘርፉ አመርቂ ውጤት እንዲመጣ ማድረጉን አመልክተዋል።

በተጀመረው የ2010 በጀት ዓመትም ከአጎራባች ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ሰላም ለማረጋገጥና ልማቱን ለማፋጠን እንደሚሰራም አቶ ወንድአፍራሽ አመልክተዋል።

የዞኑ ፀጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢና የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ በ2009 ዓ.ም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎች ሽልማት ሰጥተዋል።

የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር ለህገመንግስቱ የበላይነትና ለህዝብ የሚቆም ፖሊስ ለመገንባት የተጀመረው ጥረትም ተጠናክሮ አንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች በተለያዩ ደረጃ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶች መኖራቸውን ገለጸው፣ የውጪና የሀገር ውስጥ  ባለሀብቶች ወደአካባቢው መጥተው ቢያለሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሚኒሻ፣ ከፖሊስ፣ ከፀጥታና አስተዳደር የላቀ የሥራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ወረዳዎች የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ