አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የሰሜን ጎንደር አስተዳደራዊ አወቃቀር የህዝቡን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንዳለው ተገለጸ Featured

12 Sep 2017
610 times

ጎንደር መስከረም 2/2010 የሰሜን ጎንደር አስተዳደራዊ አወቃቀር የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡

ነባሩ አስተዳደራዊ አወቃቀር ከዞኑ የቆዳ ስፋት፣ ከህዝቡ ቁጥር፣  ከመልካ ምድር አቀማመጥ አንጻር የህብረተሰቡን የልማትና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መንገድ ለማዳረስ  አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉአለም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት በነባሩ ዞን አንድ የወረዳ ቀበሌ ከርቀቱና ከመልካምድራዊ አቀማመጡ አስቸጋሪነት የተነሳ በስድስት ወር አንድ ጊዜ እንኳን የፍትህም ሆነ አስተዳደራዊ አገልግሎት ድጋፍ እንደማያገኝ ነው፡፡

በዞኑ ህዝቡ በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩ የቀበሌና የወረዳ ይከፈልልን ጥያቄ በመፍታት በኩል በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ለአብነትም የ103 የቀበሌዎችና የአራት ወረዳዎች   ጥያቄ  መፍታት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አየልኝ እንዳሉት ነባሩን ዞን በሶስት አስተዳደራዊ ዞኖች የማዋቀር ጥያቄ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን በአመራሩና በህዝቡ ለክልሉ መንግስት ጥያቄው ቀርቦ ነበር፡፡ 

የክልሉ መንግስት አስተዳደራዊ መዋቅሩ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን እንደሚተገበር በገባው ቃል መሰረት በተያዘው አዲስ ዓመት አስተዳደራዊ መዋቅሩን ወደ ሙሉ ትግባራ ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

"አዲሱ አስተዳደራዊ አወቃቀር ማዕከላዊ ጎንደር ፣ምዕራባዊ ጎንደርና ሰሜናዊ ጎንደር በሚል የተዋቀረ ነው " ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ጎንደር ከተማ ፣ ገንዳውሃና ደባርቅ የዞኖቹ ዋና ከተሞች  ናቸው፡፡

አዲሶቹን ዞኖች የሚያስተባብሩ አስተዳዳሪዎችና ምክትላቸው እንደተመደቡም ጠቅሰዋል፡፡

ለዞኖቹ የሚያስፈልገውን ዓመታዊ የልማት በጀት ፣ የአመራርና የባለሙያዎች ምደባ በየደረጃው ተፈጻሚ የሚደረግ ሲሆን ነባሩ ዞንም የቅርብ ድጋፍ በመስጠት አዲሶቹን ዞኖች የማጠናከር ስራ የሚያከናውን ይሆናል፡፡

ለዞኖቹ አስተዳደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሶስት ዘመናዊ ህንጻዎችም የአካባቢውን ባህልና ታሪክ ወካይ በሚሆን የህንጻ ዲዛይን ተሰርቶ ለግንባታ እየተዘጋጁ ናቸው፡፡

በአዲሱ ዓመት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና አስተዳዳሪው ጠቁመው አዲሱ አስተዳደራዊ መዋቅር የህዝቡን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ነባሩ የሰሜን ጎንደር አስተዳደራዊ አወቃቀር ከክልሉ የቆዳ ስፋት 26 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖርበት ነው፡፡

ነባሩ ዞን ከባህር ጠለል 4ሺ 620 ሜትር ከፍታ ካለው የራስ ዳሽን ተራራ ጀምሮ እስከ 400ሜትር ዝቅተኛ የመልክአ ምድር አቀማመጥ የሚገኝበት ስፍራ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡       

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ