አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ቀን በመላው አገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው

10 Sep 2017
738 times

ማይጨው/አዲስአበባ ጳጉሜ 5/2009 የኢትዮጵያ ቀን በመላው አገሪቱ ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው።

በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ዕለት የኢትዮጵያ ቀን እንዲከበር መንግስት በወሰነው መሰረት በዓሉ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ የመልካም ምኞት መግለጫ ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

"መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው " በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ቀን ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር በመዲናዋ ዝግጅት ላይ ደግሞ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ተጋባዥ  እንግዶች ይታደሙበታል።

በዓሉ በማይጨው ሲከበር ወጣቱ አባቶች ያስረከቡትን ሀገር በመጠበቅ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን  ማጠናከር እንዳለበት የከተማዋ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ ቀን ምክንያት በማድረግ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት ወጣቱ ትውልድ ከጥንት አባቶቹ የወረሰውን ሉአላዊ ሀገር ጠብቆ የማቆየት ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ።

የከተማው ነዋሪ አቶ አበበ ጓንጉል እንዳሉት ከጥንት ጀምሮ  ጀግኖች አባቶች  ወራሪዎችን  በመመከት ለሀገሪቱ ሉአላዊነት መከበር የከፈሉት መስዋዕትነት የማይረሳና ታሪክ የማይሽረው ነው።

ኢትዮጵያ  ከራሷዋ ድንበር ማስከበር አልፋ እንደ ኮሪያ፣ ሩዋንዳና ደቡብ ሱዳን በመሳሰሉ ሀገራት በሰላም ማስከበር ላይ በመሳተፍ  አለም አቀፍ  ተልዕኮዋን እንደተወጣችም አውሰተዋል ።

"ኢትዮጵያ  ከድርቡሽና ከዶግዓሊ ጦርነት ጀምሮ በተከታታይ የተካሄዱ ወረራዎችን በልጆቿዋ ተጋድሎ መክታ ነፃንቷን ያስከበረች ሀገር ናት" ብለዋል ።

የአሁኑ ትውልድ የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖረውም የሀገሩን ሉዓላዊነት በመጠበቅ  ከአባቶቹ  የወረሰውን አደራ ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታላቅ ተጋድሎ ወራሪዎችን በማሳፈር ነፃነቷን ያስከበረች ሀገር መሆኗን የተናገሩት ደግሞ  ሌላው ነዋሪ መምህር በርሄ በላይ ናቸው። 

"ሀገራችን በንጉሰ ነገስቱ ጊዜ በኮንጎ የሰላም ማስከበርና በደርግ ዘመነ መንግስትም ቢሆን ለዝምባቤ  ነፃነት መከበር የከፈለችው ዋጋ  የልጆችዋ  የጀግንነት መስዋዕትነት ውጤት ነው " ብለዋል ።

"ከደርግ ውድቀት በኋላም  የአሁኑ የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን የአፍሪካ ህዝቦችን ጠበቃ ለመሆን በቅቷል"  ያሉት መምህር በርሄ ሰራዊቱ  ኢትዮጵያ የአፍሪካ  ህዝቦች የሰላም ማስከበር ግዳጅን በብቃት በመወጣት አለም አቀፍ ዝና እንዲኖራት ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ ትውልድም  ምንም እንኳን የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረውም  በሀገሪቱ ያለውን የተመቻቸ ሁኔታ ተጠቅሞ  የሀገሩን  አኩሪ ገድልና ታሪክ በጋራ ጠብቆ ማቆየት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል፡፡ 

ወጣቱ የጀግኖች አባቶቹን ታሪክ ጠበቆ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን  ማጠናከር እንዳለበት ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ