አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለተ ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እንዲችል በአዋጁ አዲስ አንቀፅ እንዲካተት ተስማሙ Featured

12 Aug 2017
679 times

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2009 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መንግስት ፓርቲዎቹ የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ የሚውል ድጋፍ ለማድረግ እንዲችል በምዝገባ አዋጅ አዲስ ንኡስ አንቀፅ እንዲካተት ተስማሙ።

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ላይ ሲያካሂዱ የቆዩትን ድርድር ዛሬ አጠናቀዋል።

ፓርቲዎቹ በአዋጁ ከአንቀፅ 42 እስከ 63 የተዘረዘሩት ስለፖለቲካ ፓርቲዎች የገቢ ምንጭ እና የንብረት ሁኔታ፣ የተከለከሉ ተግባራት እና የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ላይ ድርድር አድርገዋል።

ፓርቲዎቹ ባካሄዱት ድርድር  መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማስኬጃ የሚውል ድጋፍ የሚያደርግበት አዲስ ንዑስ አንቀፅ እንዲካተት ተስማምተዋል። 

የሚድያ ኮሚቴ አባልና የኢዴህ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ እንዳሉት፤ በአዋጁ ቁጥር 573/2000 መሰረት ቀደም ብሎ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ የሚሰጠው ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ውድድር በሚያካሂዱበት ወቅት ለሚያከናውኗቸው ተግባራት የሚውል ነበር።

ዛሬ ባከሄዱት ድርድር ፓርቲዎቹ  በደረሱበት ስምምነት መሰረት መንግስት በየዓመቱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ የሚውል ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችለው አዲስ ንዑስ አንቀፅ ይካተታል፡፡ 

በዚህ መሰረት ከአባላት መዋጮ፣ ከዜጎችና ከአገር በቀል ኩባንያዎች የሚሰጥ ድጋፍና በሚያካሄዱት ባዛር ከሚገኝ ገቢ በተጨማሪ በሚካተተው ንዑስ አንቀጽ መሰረት "መንግስት የሚሰጠውን የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ድጋፍ ያገኛሉ" ብለዋል።

ፓርቲዎች ይሄን ድጋፍ የሚያገኙት በአዋጁ አንቀፅ 45 ንኡስ አንቀፅ 2 መሰረት "ባገኙት ድምፅና ባቀረቡት ዕጩ ብዛት፣ ባቀረቡት የሴቶች ዕጩ ብዛትና በምክር ቤት ባላቸው ወንበር መሰረት ይሆናል" በሚል እንዲሻሻል ተደርጓል።

የሚድያ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምበሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው የምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት እንደሚከናወን ጠቁመው በዚህም አዋጁ አንቀፅ 45 ንኡስ አንቀፅ 4 እንዲሻሻል መደረጉን ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ በምርጫ ቦርድ ፓርቲዎችን የመሰረዝ ስልጣን ላይ ሰፊ ድርድር አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ፓርቲዎችን የመሰረዝ ስልጣን የቦርዱ ሆኖ ባለበት እንዲቀጥል በተባበረ ድምፅ ተስማምተዋል።

በአዋጁ ልዩ ድንጋጌዎች ውስጥ ከተዘረዘሩት አንቀጾች መካከል አንቀፅ 59 የምርጫ ቦርድ በከፊል የዳኝነት ስልጣኑ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሳይፈፀሙ ቢቀር በራሱ የሚወስናቸው እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው "ቦርዱ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አፈፃፀም ከፍቶ ሊያስፈፅም ይችላል" በሚል እንዲሻሻል ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ በዛሬው ድርድራቸው ፓርቲዎች ጽህፈት ቤት እንዳይኖራቸው የሚያደናቅፉ አካላት በህግ የሚጠይቁበት አንቀፅ እንዲካተትም ተስማምተዋል።

እንዲሁም አንቀፅ 55 ንኡስ አንቀፅ 3 ላይ “ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል በማንኛውም ጊዜ ለስራ መሰናክል ሳይሆን አባል የሆነበትን የፓርቲውን የገቢና ወጭ ሂሳብ መረጃ የማግኘት መብት አለው” በሚል የተቀመጠው እንዲሰረዝ ወስነዋል።

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በርካታ የተሻሻሉና አዳዲስ አንቀፆች ተጨምረውበት የየፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጁ በረቂቅ አዋጅ መልክ ተዋቅሮ እንዲቀርብ ፓርቲዎቹ ከስምምነት ደርሰዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ ባካሄዱት ድርድር ላይ አዲስ የሚዲያ ኮሚቴ ያዋቀሩ ሲሆን፤ ከገዢው ፓርቲ አምበሳደር ደግፌ ቡላ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ እና የመላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ፀሓፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ተመርጠዋል።

ገዢው ፓርቲ የድርድሩ ቀን ይራዘም በማለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ቀጣዩ ድርድር መስከረም የመጀመሪያ ሳምንት ላይ በምርጫ ህጉ አዋጅ 532/1999 ድርድሩ እንዲቀጥል ተስማምተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ