አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የኢትዮጵያንና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ህዝቦችን ወዳጅነት እናጠናክራለን---የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት የልኡካን ቡድን Featured

12 Aug 2017
443 times

ባህር ዳር ነሐሴ 5/2009 በኢትዮጵያና በሶማሊያ ሪፐብሊክ ህዝቦች መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ወዳጅነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተግተው እንደሚሰሩ የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት የልኡካን ቡድን አባላት ገለፁ።

የልኡካን ቡድኑ አባላት ከአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ጋር በፌደራሊዝም ስርዓት አወቃቀር ዙሪያ በባህር ዳር ከተማ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

የቡድኑ መሪ አብድላሂ መሃመድ በልምድ ልውውጡ ላይ እንደገለፁት ሃገራቸው ከ26 ዓመታት በላይ ከዘለቀ ብጥብጥና ሁከት በኋላ እንደ ሃገር አንድ ሆና የሚያስቀጥላትን ስርዓት በመዘርጋት ላይ ትገኛለች።

በአሁኑ ወቅት በአንፃራዊነት የተረጋጋ ሰላም የሰፈነባትና ህዝቦቿም የእለት ተግባራቸውን የሚያከናውኑበትን ምቹ ሁኔታ ለማምጣት የተለያዩ የልማት ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የአካባቢው ሰላም መደፍረስ ያሳሰባት ጎረቤት ሃገር ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የሰላም አስከባሪ ሃይል በመላክ ለሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና ማበርከቷንም ገልፀዋል።

ሶማሊያ ሪፐብሊክን መልሶ በማደረጀትና ጠንካራ መንግስት በማቋቋም ለረጅም ጊዜ የዘለቀውንና በመርህ ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት በማጠናከር ተቀራርበው እየሰሩ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት፡፡

ሃገራቸው የፌደራሊዝም ስርዓትን በመተግበር ላይ መሆኗን ጠቁመው ለዚህም የተሻለ የፌደራሊዝም አደረጃጀት ያላት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመውስድ መወሰናቸውን አብራርተዋል።

በቆይታቸውም በተለይ በአጎራባች ክልሎች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ጠቃሚ የአፈታት ተሞክሮ ማግኘታቸውን ጠቁመው በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  መካከል ካለው ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል ጥሩ ልምድ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል አፈ-ጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው "የጎረቤት ሃገር ሶማሊያ ሪፐብሊክ  ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት የሚኖረው ሚና የላቀ ነው" ብለዋል።

የሶማሊያ ሪፐብሊክን ወደ ቀደመ ገጽታዋ ለመመለስ የፌደራሊዝም ስርዓትን መተግበሯ አዋጭ መሆኑን ጠቁመው፤ ከኢትዮጵያ የሚወሰደው የፌደራሊዝም ተሞክሮ እንዳለ ሆኖ የህዝቦቿን ልምድ፣ አኗኗርና ባህል መሰረት በማድረግ ሊተገበር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ሃገሪቱን መልሶ በማደረጃትና የተረጋጋች የልማትና የእድገት ቀጠና እንድትሆን በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የአማራ ክልላዊ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

በባህር ዳር ከተማ ዛሬ በተደረገው የልምድ ልውውጥ የክልሉ የምክር ቤት አወቃቀርና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴ ልምድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

25 አበላትን የያዘው የልዑካን ቡድን የአማራ ህዝቦች ሰማዕታት ሃውልትና የቤዛዊት ቤተ-መንግስትንና የአማራ ክልል ምክር ቤት ህንፃን እንዲጎበኙ የተደረገ ሲሆን ለልዑካን ቡድኑም ሙሉ የባህዕል አልባሳት ተበርክቶላቸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ