አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ሶስት አገራት ስምምነቱን ካጸደቁት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ይቋቋማል Featured

12 Aug 2017
520 times

አዲስ አበባ ነሀሴ 5/2009 ተጨማሪ ሶስት የተፋሰሱ አገራት የትብብር ስምምነት ማዕቀፉን ሲያጸድቁት የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እንደሚቋቋም የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ የናይል ወንዝ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ መኖር አለበት የሚለውን መርህ በመደገፍ ስምምነቱን አጽድቀዋል።

የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል የናይልን ወንዝ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ያስችላል ተብሏል።

የናይልን ወንዝ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኙ የተፋሰሱ አገራት እ.ኤ.አ በ 1999 የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭን አቋቁመዋል።

በወንዙ ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ለማቋቋም እ.ኤ.አ. በ 2010 ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ቡሩንዲ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን ተቀብለዋል።

የምስራቅ ናይል ቴክኒካል አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት የተፋሰሱ አገራት የዓባይን ወንዝ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀም የሚያስችላቸውን የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ለማቋቋም የሶስት አገራት ስምምነቱን የማጽደቅ ውሳኔ ብቻ ይቀራል።

ስምምነቱን የተቀበሉት አራት አገራት ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲ፣ ኬንያና ኡጋንዳ ስምምነቱን ለማጽደቅ በሂደት ላይ እንደሆኑና ሶስቱ ካጸደቁት ኮሚሽኑ ተቋቁሞ አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍም እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

በመሆኑም ስምምነቱን የተቀበለችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ አለመፈረም፣ የሱዳንና ግብጽ አለመቀበል ኮሚሽኑን ከመቋቋም አያግደውም፤ ነገር ግን በማንኛውም ጊዜ ስምምነቱን በማጽደቅ የኮሚሽኑ አካል መሆን ይችላሉ ብለዋል።

"የናይል ተፋሰስ አገራት የሚመሩበት የህግ ማዕቀፍ የለም፣ ይህ ደግሞ ውሃውን በዘፈቀደ እንዲጠቀሙና አገራት ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዲገቡ ያደርጋል፤ ተፋሰሱም ይጎዳል" ነው ያሉት አቶ ፈቅአህመድ።

 አስገዳጅ የህግ ማዕቀፉ የተፋሰሱ አገራት ውሃውን ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀምና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዲችሉ ያግዛልም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው ሱዳንና ግብጽ ስምምነቱን ባለመቀበላቸው ጉዳት እንጂ የሚያገኙት ጥቅም የለም ይላሉ።

ስምምነቱን ያልፈረሙ አገሮች ውሃውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም እንደሚቸገሩና ያጸደቁት አገሮች ራሳቸውን በሚጠቅም መንገድ የማልማት ብሄራዊና ሉዓላዊ መብት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ