አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የአዋጁ መነሳት የተሻለ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ይረዳናል -የፖለቲካ ፓርቲዎች

12 Aug 2017
449 times

አዲስ አበባ ነሃሴ 5/2009 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅት እንደሚረዳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።

ከአንድ ዓመት በፊት ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በመደበኛ የህግ ማስከበር ማስቆም ባለመቻሉ አገሪቱ ላለፉት 10 ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ቆይታለች።

የአዋጁን መነሳት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ መኢብን፣ኢዴፓ፣መኢዴፓ እና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር አባላት፤ የአዋጁ መነሳት የተሻለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግና ለቀጣዩ ምርጫ ለመዘጋጀት እንደሚረዳቸው ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት ባከናወናቸው ሥራዎች በመደበኛ አሰራር ህግ ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ መንግስት አዋጁ እንዲነሳ ማድረጉ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ፓርቲዎቹ ገልፀዋል።

አዋጁ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴና በመጪው ዓመት ለሚካሄደው የማሟያ ምርጫ የሚያደርጉት ዝግጅት ላይ ተፅእኖ ፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በመደበኛ አሰራር ህግ ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ በመፍጠሩ የአዋጁ መነሳት ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) አቶ መሳፍንት ሽፈራው እንደገለፁት፤ በመደበኛ አሰራር ህግ ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ አዋጁ መነሳቱ ተገቢ ነው።

ይሄም በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ "ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ "ሁከት እና ብጥብጡን ለማስቆም የተቀመጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሮብን ነበር" ብለዋል።

አዋጁ መነሳቱም የፖለቲካ ምህዳሩን በመጠቀም ፓርቲን በማጠናከር የተሻለ እንቅስቃሴ እንድናደርግ ዕድል ይፈጥርልናል ነው ያሉት።

የመላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) ዋና ፀሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ በበኩላቸውም፤ በየክልሉ ያሉ አባሎቻቸውን ለማግኘትና ለማጠናከር አዋጁ ተግዳሮት ሆኖባቸው እንደቆየ ነው የሚያስረዱት።

አሁን ግን አዋጁ በመነሳቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ በመጠቆም።

"አዋጁ ዓላማውን አሳክቶ በወቅቱ መነሳቱ ለሚቀጥለው ማሟያ ምርጫ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል" ያሉት ደግሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ትግስቱ አወሉ ናቸው።

ፓርቲዎቹ በሰጡት አስተያየት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት መፍጠሩን ተናግረዋል።

ላለፉት 10 ወራት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደበኛ አሰራር ህግ ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን በመገምገም ባሳለፍነው ሳምንት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁ እንዲነሳ ማድረጉ ይታወሳል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ