አርዕስተ ዜና

ለአፍሪካ ወጣቶች ተጠቃሚነት የአቅም ግንባታ ስራዎች መጠናከር አለባቸው ተባለ

11 Aug 2017
319 times

አዲስ አበባ ነሃሴ 5/2009 የአፍሪካ ወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አገራት የአቅም ማጎልበት ሥራ ላይ በሥፋት መሥራት አንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት ያልተማከለ ቀን "የእናንተ ተሳትፎ" በሚል መሪ ኃሳብ በትላንትናው ዕለት በሞሮኮ መዲና ራባት ተከብሯል።

በአፍሪካ ከ63 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ሲሆን አማካይ እድሜው ደግሞ አስራ ዘጠኝ ነው።

ይህም ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ ህዝብ ቁጥር 200 ሚሊዮን የሚሆነውን በመያዝ፣ በቀጣይ 20 ዓመታት ውስጥ 500 ሚለዮን ይደርሳል ተብሏል።

ከእነዚህ መካከል 72 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በቀን ከሁለት ዶላር በታች ገቢ የሚያገኙ ሲሆን በዓመቱ ደግሞ በአህጉሪቱ ከ10 አስከ 12 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ እድሜን ይቀላቀላሉ።

በአፍሪካ በአሁኑ ወቀት እድሜያቸው ከ6 እስከ 14 የሆኑ ሕጻናትም በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲሆኑ በዚህም በአፍሪካ ከተሞች በርካታ ህጻናት ከመጠለያ ውጭ በመሆን ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ጎዳና ላይ አንዲኖሩ አስገድዷል።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራትም ከአምስት ወጣቶች ሦስቱ ሥራ አጥ መሆናቸውን የዓለም የሥራ ድርጅትና የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ ሪፖርት ያሳያል።

ይህንንም ከግምት በማስገባት የአፍሪካ ኅብረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2009 እስከ 2018 ያሉትን ዓመታት የአፍሪካ ወጣቶች ዓመታት ብሎ ሰይሞታል።

ይሁንና ይህ የፖለቲካ ድንጋጌ በአህጉሪቱ ባሉ የተለያዩ ችግሮች በወጣቶች ላይ ለማምጣት የወጠነውን ውጤት ሳያስመዘግብ ድንጋጌው ሊጠናቀቅ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በዚህም የተነሳ ወጣቶች ለከፍተኛ የሥነ-ልቦና ቀውስና ተሰፋ ማጣት ሁኔታ ውስጥ አንዲዘፈቁ ግድ ብሏል።

በመሆኑም የአፍሪካ ሴት የከተሞች ከንቲባና ተመራጭ ሴቶች ትስስር የሚባል ቡድን 'የአፍሪካ ከተሞች ከጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ውጪ' የሚል መርኃ ግብር ይፋ አድርጓል።

በዚህም ወጣቶችን ማብቃት የሚያስችል የወጣቶች አቅም ማጎልበቻ መርኃ ግብር በመንደፍ በወጣቶች ላይ የሚስተዋሉትን ማለትም ሥራ አጥነትን መቅረፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተጓዳኝም የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲያዳብሩ፣ በትምህርት፣ በባህል፣ በጥበብ፣ በቅርስ፣ በስፖርትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ወጣቶች  ተሳታፊና ተጠቃሚ አንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም አገራት ለወጣቶች አዳዲስ እድሎችን በማቅረብ የመሪነት ሚናውን መጫወት አንዳለባቸው አሳስበዋል።

አገራት ግልጽ የሆነ አሰራር በመንደፍ ወጣቶች በሚኖሩበት ከተማ ያሉትን የምክር ቤት አባላትና አስተዳዳሪዎችን አንዲያገኙ ማመቻቸት አንደሚጠበቅባቸውም አንዲሁ።

በከተሞች አከባቢ ወጣቶችን ያቀፈ ምክር ቤት በማቋቋም፤ ወጣቶች የከተሞችን ኃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን መረዳት አንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።

ወጣቶች የሚሳተፉባቸው መድረኮችን በማዘጋጀት የሥራ ኃላዎች ከወጣቶች ኃሳብ በመሰብሰብ የህዝቡን ኑሮ ወደ ኋላ የሚጎትቱ እንቅፋቶችን በመለየት እልባት መስጠት እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ቡድኑ በተለይም የሚወጡ መርኃ ግብሮችና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ