አርዕስተ ዜና

ለዴሞክራሲዊ ስርዓት መጎልበት የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ---ምሁራን

19 Jun 2017
556 times

መቀሌ ሰኔ 12/2009 በሀገሪቱ የዴሞክራሲዊ ስርዓትን ለማጎልበት  የሲቪክ ማህበራትና የህብረተሰቡ  ተሳትፎ  ሊጠናከር  እንደሚገባ በመቀሌ፣ በአዲግራትና በአክሱም ዩኒቨርስቲዎች አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን አመለከቱ፡፡

 ከምሁራኑ መካከል በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስነዜጋና ስነምግባር መምህር ሸዊት ገብረእግዚአብሄር ለኢዜአ እንዳሉት በአንድ አገር የዴሞክራሲ ስርዓት ሂደት መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።

 ይሄውም የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ በህገመንግስቱና ከዚህ በመነጩ የህግ ማዕቀፎች መረጋገጡ በሀገሪቱ  የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንደሚያመለክት ተናግረዋል፡፡

 እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ሲቪክ ማህበራትና ህብረተሰቡ  የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ  መፋጣን ወሳኝነት አለው፡፡ 

 " ዴሞክራሲያዊ መንግስት የምንፈልግ ከሆነ እንዲኖርም እንዳይኖርም የምናደርገው ራሳችን በምናደርገው ተሳትፎ ይወሰናል፤  ዜጎች  በተለያየ እርከን ከታች ከወረዳው ጀምሮ እስከ ላይ ባሉት የመንግስት መዋቅሮች ላይ በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል" ብለዋል መምህር ሸዊት።

 ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መገለጫዎች መካከል የዜጎች እኩልነት፣ በነፃ የመደራጀትና ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች መከበር እንደሚገኙበት የተናገሩት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስነ ምግባርና ስነ ዜጋ መምህርት ሶስና አዳነ ናቸው፡፡

 ዜጎችና የኃይማኖት  እኩልነት  መኖር  ተከባበረው  ለሀገራዊ እድገት በጋራ እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡

 መምህርት ሶስና እንዳሉት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  ተማሪዎችና ሌላው ማህበረሰብ  በጋራና በእኩልነት አብሮ መንቀሳቀስ  ጎልቶ የሚታይባቸው ናቸው፤ በእነዚህም ዴሞክራሲ ስርዓት  ለማዳበር የሚያስችሉ ስራዎች በቀጣይነት መስራት አለበት፡፡

 በዓዲግራት ዩንቨርስቲ የስነዜጋና ስነምግባር መምህር ወልደአብርሃ ንጉስ በበኩላቸው "የሲቪክ ማህበራትና በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት  አባላት ለዴሞክራሲ  ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን  ሚና እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

 መንግስት ባለፉት 26 ዓመታት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎች ያስቀመጠ ቢሆንም የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር የተከናወኑ ስራዎች ግን የተፈለገውን ያህል አለመሆኑን ገልጸዋል።

 "  በዴሞክራሲ የምናገኘው ውጤት ልክ የዘራነውን  እንደምናጭድ ያህል የሚቆጠር ነው " ያሉት መምህሩ  በተለያዩ አካባቢዎች አልፎ አልፎ እየታዩ ያሉት የመልካም አስተዳደርና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በቀላሉ ሊታዩ እንደማገባም ጠቅሰዋል፡፡

 በአክሱም ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዶክተር ነጋ ሰለሞን እንዳሉት ደግሞ  የሃሳብ ልዩነት የሚስተናገድበት ብዙሃነትን ማጠናከር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊ ነው።

 ዩኒቨርስቲዎች የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  መገለጫ በመሆናቸው ለዴሞክራሲ መጎልበት የበኩላቸው ሚና እየተጫወቱ  መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ ላይ  የህብረተሰቡም ድርሻና ተሳትፎ  ሊጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ