የአገሪቱን ህዳሴ እውን ለማድረግ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው

18 Jun 2017
425 times

ጋምቤላ ሰኔ 11/2009 የሀይማኖት አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በመታገል የአገሪቱን ህዳሴ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ወጣቱ ግንባር ቀደም ሚናውን መወጣት እንዳለበት የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚንስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴር መስሪይ ቤቱ ከኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ የወጣትና ሴት አደረጃጀቶች ሥልጠና ሰጥቷል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰላምና መከባበርን ማስፈን ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ዱቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በሀገሪቱ በተለያዩ ሀይማኖቶች መካከል አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶችን የሚሸረሽሩ እንቅስቃሴዎች  ይታያሉ።

በመሆኑም እነዚህን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመዋጋት የተጀመረውን የልማትና የህዳሴ  ጉዞ ለማስቀጠል ከወጣቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልል ጉዳዮች ዋና መምሪያ ኃላፊ መጋቢ ይታገሱ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሰላምና አብሮ የመኖር እሴትን ለማደፍረስ የሚሞክሩ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ሁኔታ ለመከላከል እና በሀገሪቱ ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴት እንዲጠበቅ ለማድረግ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የተጀመሩ ሥራዎችን ለማሳካት ወጣቱ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመው ሥልጠናውም የወጣቱን ግንዛቤ በማሳደግ በሰላም እሴት ግንባታው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል ወጣት ብሊም ኡዶል በሰጠው አሰተያየት በአክራሪነትና በጽንፈኝነት ዙሪያ የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ እንደነበር ገልፆ በስልጠናው ያገኘውን ግንዛቤ ለህብረተሰቡ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

በጽንፈኝነትና አክራሪነት ዙሪያ ያገኘውን ስልጠና ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ሌላው የሥልጠናው ተሳታፊ  ወጣት አቤል ኡቻላ ነው።

ላለፉት ሁለት ቀናት በጋምቤላ ከተማ የተሰጠው ስልጠና በኢፊዴሪ ህገ-መንግስት፣ በሃይማኖት ብዝሃነት፣ አያያዝና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡ 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ