አርዕስተ ዜና

የሁለንተናዊ ዕድገቱ መሰረት በሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ህዳሴ ይረጋገጣል-የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት Featured

20 May 2017
883 times

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የፌዴራላዊ ሥርዓቱ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሃገሪቱን ሕዳሴ ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አሳሰበ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ዛሬ በላከው ሳምንታዊ የመንግስት አቋም መግለጫው ላይ እንዳስታወቀው ''የሕዝቦችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ስርዓት እየገነባች ያለች ሀገር-ኢትዮጵያ'' በሚል መሪ መልእክት በቅርቡ የሚከበረው 26ኛው የግንቦት ሃያ ድል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ላቅ ያለ ክብር ይሰጠዋል ብሏል፡፡

ሀገሪቱ የተጓዘችባቸው ዓመታት ሁሉ አልጋ በአልጋ ያልነበሩ ቢሆንም እድገቷን የሚፈታተኑ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች በየጊዜው እያጋጠሙዋት እያለፈች እንደመጣችም አመላክቷል፡

ለተግዳሮቶች መፍትሔዎችን እያበጀ የመጣውም የፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሥርዓቱ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው በቀጣይም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተመሳሳይ መልኩ ስርዓቱ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ እየተፈቱ እንደሚሔዱም እንደማያጠራጥር አረጋግጧል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

የሁለንተናዊ ዕድገታችን መሰረት በሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓታችን ህዳሴያችንን እናረጋግጣለን!

አገራችን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነታቸው ተከብሮላቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማስቻሉ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲፈጥሩ አድርጓል። በአገራችን አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍንም አስችሏል።  ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመልማት መብታቸውን እንዲጠቀሙና ሁሉም አካባቢዎች እንዲለሙ አስችሏል። ልማቱ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑም ሌላው ተጨባጭ ዕውነታ ነው።

ከ26 ዓመታት በፊት አንዳችም የመሠረተ ልማት እና ማህበራዊ ተቋማት ባልነበረባቸው አካባቢዎች ዛሬ የእነዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን የዘወትር ትዕይንት ሆኗል። ለአብነት አገራችን የትምህርት ሽፋንና የጤና አገልግሎትን በማስፋፋት የተባበሩት መንግስታትን የልማት ግቦችን ማሳካት የተቻለው በሁሉም አካባቢ በፍትሃዊነት በተከናወነ ሥራ እና በተገኘ ውጤት ነው። በህዝቦች የላቀ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚካሄደው ልማታችን ድምር ውጤቱም ዛሬ አገራችንን በምዕራቡ ዓለም የአፍሪካዋ ነብር ወይም አንበሳ በሚሉ ስያሜዎች እንድትወደስ ያስቻለ ነው። 

ዛሬ እንደ አገር ባለራዕይ ህዝብ ሆነን ወደ ህዳሴ ማማ ለመውጣት ሽቅብ በመጓዝ ላይ እንገኛለን። ከራሳችን አልፈንም የምስራቅ አፍሪካን አገራት በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር አልመን እየሰራን እንገኛለን።

ከ26 ዓመታት በፊት በረሃብ ትታወቅ የነበረችው አገራችን አሁን ላይ የምትታወቀው በፈጣን የኢኮኖሚ እድገቷ ሆኗል። ከአብዛኛው የዓለም አገራት ተነጥላ የነበረችው አገራችን አሁን ላይ የምትታወቀው የዲፕሎማሲ ቁንጮ እና የአፍሪካ መግቢያ በር በመሆን ነው። በእርስ በርስ ጦርነት አውድማነት ትታወቅ የነበረችው አገራችን አሁን ላይ የምትታወቀው የአፍሪካ አገራት መፍትሄ አፈላላጊና ቃል አቀባይ እንዲሁም የሰላም አስከባሪ እና ተደራዳሪ በመሆን ነው። ለአብነት በቻይና በተካሄደው የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ ጉባዔ ላይ አፍሪካን ወክላ የቀረበችው አገራችን ኢትዮጵያ ናት። አሁን አሁን ደግሞ የዓለም ታላላቅ ግዙፍ ኩባንያዎች መዳረሻ፣ የቱሪስቶች እና የትላልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች መናገሻ በመሆን እየታወቀች መጥታለች።

እጅግ ከብዙ በጥቂቱ ለማሳያነት ከላይ ከቀረቡት ሁለንተናዊ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሁሉ በስተጀርባ ያለው ዋነኛ ምስጢር ግንቦት ሃያ ያመጣልን የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ነው! ለአስተማማኙና ፈጣኑ እድገታችን ጽኑ መሰረት የሆነው ይህ ስርዓታችን የቀጣዩ እድገታችንም ዋስትና መሆኑንም ለመገንዘብ አያዳግትም። በመሆኑም “የህዝቦች እኩልነትና  ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ስርዓት እየገነባች ያለች ሀገር - ኢትዮጵያ” በሚል መሪ መልዕክት በቅርቡ የምናከብረው 26ኛው የግንቦት ሃያ ድል በዓል በኢትዮጵያውን ዘንድ ላቅ ያለ ክብር ይሰጠዋል።

እርግጥ የተጓዝንባቸው ዓመታት ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። እድገታችንን የሚፈታተኑ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች በየጊዜው እያጋጠሙን እያለፍናቸው መጥተናል። ላጋጠሙን ተግዳሮቶች ሁሉ መፍትሄዎቹን ያበጀልንም ይኸው የምንከተለው የፌዴራላዊ ሥርዓታችን ነበር። በቀጣይም የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተመሳሳይ መልኩ እየፈታን መሄዳችን አያጠራጥርም።

 በመሆኑም መላው ኢትዮጵያውያን የፌዴራላዊ ሥርዓቱ በፈጠረልን ምቹ ሁኔታ  እጅ ለእጅ ተያይዘን አገራችንን በህዳሴዋ ማማ ላይ ለማስቀመጥ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ይገባናል። በብዝሃነት የደመቀው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የህዳሴያችን ዋስትና ነውና!

የኢፌዲሪ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ