አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ፓርቲዎቹ ያቀረቧቸው የመወያያ ሃሳቦች በትክክል ለአጀንዳ ኮሚቴ መድረሳቸውን አረጋገጡ

19 May 2017
779 times

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2009 የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመደራደር ያቀረቧቸው ሃሳቦች ለአጀንዳ ኮሚቴው መድረሱን አረጋገጡ።

ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው ሁለት ታዛቢ እንዲያቀርቡም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያካሄዱት ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ላይ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እየተወያዩ ናቸው።

በዛሬው ዕለት እያንዳንዱ ፓርቲ ባለፉት 15 ቀናት ያቀረባቸውን ሃሳቦች ለአጀንዳ ኮሚቴው መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

የአጀንዳና የሚዲያ ኮሚቴ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት ፓርቲ /ኢዴህ/ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ከውይይቱ በኋላ እንዳሉት ፤ የአጀንዳ ኮሚቴው ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ከ17 ፓርቲዎች የተቀበላቸውን የመወያያ ሃሳቦች ሳይጨመርና ሳይቀነስ ለፓርቲዎቹ አቅርቧል።

ፓርቲዎቹ እያንዳንዳቸው ከ1 እስከ 34 የሚደርሱ የመወያያና የመደራደሪያ ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ በይዘታቸው ከፖለቲካ ምህዳር መጥበብ እስከ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ድረስ የሚሸፍኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በዛሬው ስብሰባቸው ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳልነበራቸው ነው የገለጹት።

ከቀረቡት ሃሳቦችና አጀንዳዎች መካከል የአጀንዳ ኮሚቴው ለድርድርና ለውይይት የሚቀርቡትን ሃሳቦች ጨምቆ ለቀጣይ ስብሰባ እንዲያቀርብ መስማማታቸውም ተመልክቷል።

ፓርቲዎቹ በቀጣይ በሚካሄዱት የድርድር፣ ክርክርና ውይይት መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ታዛቢዎች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ፓርቲ ሁለት ታዛቢዎች እንዲያቀርቡ ተወስኗል።

ፓርቲዎቹ በራሳቸው ከሚያመጧቸው ታዛቢዎች በተጨማሪ በሁሉም ፓርቲ ስምምነት መሰረት ገለልተኛ የሆኑ 12 የውጭና የአገር ውስጥ ድርጅቶች በታዛቢነት እንዲሳተፉ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዚሁ መሰረትም አምስት የሚሆኑት ከውጭ እንደሚሆኑም ታውቋል።

ታዛቢ ድርጅቶቹ ከኢምባሲዎች፣ ከሲቪክ እና ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች የተውጣጡ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል። እንደድርጅቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ከአንድ እስከ አምስት ተወካዮች የሚኖሯቸው ሲሆን፤ በመንግስት በኩል ጥሪ እንደሚደረግላቸው ታውቋል።

ዋናው ድርድር ሲጀመር እስከ ታዛቢዎቹ ከአንድ መቶ በላይ ተሳታፊዎች የሚኖሩት ይሆናል። ከአንድ ወር በማያንስ ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ማጠቃለያ ላይ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ በአገሪቷ በህጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ማድረግ ነው። በአሁኑ ወቅትም ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ 17 ፖለቲካ ፓርቲዎች ህግና ደንቡን ተከትለው በቅድመ ሁኔታዎቹ ላይ  እየተወያዩ ይገኛል።

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ