አርዕስተ ዜና

ኮርፖሬሽኑ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሻርለት ጠየቀ

19 May 2017
1350 times

አዲስ አበባ ግንቦት11/2009 የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቀድሞው የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቤቶችን ለማልማትና ለማስተላለፍ የሚፈቅድ ባለመሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሽርለት ጠየቀ።

የምክር ቤቱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ማፍረሻ ረቂቅ አዋጅን መርምሯል።

አዋጁ እንዲሻር የተጠየቀው የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/09 ወደ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን መቀየሩን ተከትሎ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘካሪያስ ሄርኮላ ለኮሚቴው እንደገለጹት የቀድሞው አዋጅ የተቋሙን ተግባርና ዓላማ በግልፅ የለየ አይደለም።

ተቋሙ ራሱን ችሎ እንዲንቀሳቀስ እንዳላስቻለው ጠቅሰው "አዋጅ 555/2000 የቤቶችን ጥገና ከማከናወን ባለፈ ቤት ለማልማትና ለማስተላለፍ የሚፈቅድ አልነበረም" ብለዋል።

ተቋሙ ወደ ኮርፖሬሽን ሊያድግ የቻለው ምክር ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀፅ 5 መሰረት ለአስፈፃሚ አካላት በሰጠው ስልጣን መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሁ መሰረት በመንግስት የልማት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/1984 መሰረት ከመንግስት ስራ አስፈፃሚነት ወደ መንግስት ልማት ድርጅትነት ተቀይሯል።

ይህ ሲደረግም ከ2006 እስከ 2008 ዓ.ም ያለው የተቋሙ ሂሳብ ከተዘጋ በኋላ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ ተቋሙ ከዓላማ፣ ካለው የካፒታል ማደግና የንግድ ቅርፅ ለውጥ በቀር ቀድሞ በነበረው ይዘት የሚቀጥል በመሆኑ የመሸጋገሪያ ጊዜ አላስፈለገውም።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ እንደተናገሩት ተቋሙ ወደ ኮርፖሬሽን ማደጉ ቤቶች ከማስተዳደር ባለፈ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቤቶች ባሉት ቦታዎች ላይ በመገንባት በኪራይ ብሎም በሽያጭ የማስተላለፍ ስራ ይሰራል።

ህንፃዎችን በመገንባትና በማስገንባት ለመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ለሰራተኞችና ባለሃብቶች ቤት የማከራየት ስራም ያከናውናል።

የስራው ማስፈፀሚያ ካፒታል ከመንግስት በጀት፣ ከቤቶች ኪራይና ከባንክ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን መሆኑንም አብራርተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በቀረቡት ማብራሪያዎች የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ለማቅረብ በመስማማት ውይይቱን አጠናቋል።

ተቋሙን ወደ ኮርፖሬሽን ለማሳደግ በአዋጅ 555/2000 ያልተሸፈኑ ነገሮች ምንድን ናቸው፣ በደንብ ወደ ሌላ ተቋም ከማስተላለፍ አዋጁን ማፍረስ መቅደም ነበረበት፣ ተቋሙ ወደ ኮርፖሬሽን ሲያድግ ሀብትና ዕዳው ተለይቷል ወይ የሚሉና ሌሎችም የቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ቀርበዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ