አርዕስተ ዜና

የአውሮፓ ፓርላማ ያወጣው መግለጫ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው Featured

19 May 2017
709 times

ግንቦት 11/2009 የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ በህግ ጥላ ስር ስላሉ ወገኖች የሰጠው አስተያየት የአገሪቷን የፍትህ ስርዓት ያላገነዘበ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ፓርላማው የኢትዮጵያን ሕግ በመተላለፋቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ስላለው ዶ/ር መራራ ጉዲና የፍርድ ሂደት ያወጣው መግለጫ ሚዛናዊነት የጎደለው፣ የአገሪቷን የፍትህ አካሄድ እና ስርዓት ያላገናዘበም ነው፡፡

“ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ መመስረት እንዳለበት ታምናለች” ያለው ሚኒስቴሩ፤ የአውሮፓ ፓርላማ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ ሳያገናዝብ ያወጣው መግለጫ በኢትዮጵያና በህብረቱ መካከል ላለው የትብብር መንፈስ ገንቢ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የህግ አውጭ አካሌ የሆነው የአውሮፓ ፓርላማ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ካልተገነዘቡ አባላቱ እይታ መነሳቱን ጠቁሞ፤ በዶ/ር መራራ የፍርድ ሂደት ላይ ያወጣው መግለጫ አግባብነት የሌለው መሆኑን ነው ያብራራው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ፤ የፓርላማው መግለጫ የህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማሳነስ ከመሞከር የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው አስታውቋል፡፡

ፓርላማው ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም ባደረገው ውይይት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ መሆኗን መጠቆሙን ገልጾ፤ የጎረቤት አገሮችን ስደተኞች ለማስተናገድ የምታደርገውን ጥረት ማወደሱን አትቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ለምትጫወተው ሚና አድንቆቱን ገልጿል፡፡

በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ለዓለም ፀጥታ አደጋ የሆነውን አሸባሪነት በመዋጋት በኩል የምታደርገውን ጥረት ያደነቀው የህብረቱ ፓርላማ፤ የደቡብ ሱዳን የፓለቲካ ተቀናቃኞችን ለማደራደር ቁልፍ ሚና እየተጫወተች መሆኗንም አንስቷል፡፡

የህብረቱ ፓርላማ መግለጫ በአገራችን የእድገት ጎዳና ላይ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ እንደማያሳርፍ አመልክቶ፤ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር እያደረገች ላለው ስትራቴጂያዊ ግንኙነት የሚመጥን በመከባበር፣ በጋራ ጥቅም፣ በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ እና የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ አመለካከት እንዲሰፍን በተጠናከረ መልኩ ከህብረቱ ጋር ምክክር እንደምትቀጥል አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነትን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሸጋገር ባለፈው ዓመት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፤ በዚህም ስድስት የትኩረት መስኮችን በመለየት በጋራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከስድስቱ ትኩረቶች መካከል የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ የምክከር መድረክ በያዝነው ዓመት መካሄዱ ይታወቃል፡፡

የህብረቱ የውጭ ግንኙነት እና የፀጥታ ጉዳዮች ኃላፊ ፌድረካ ሙጌሪኒ በተያዘው ዓመት ወደ አገሪቷ በመምጣት ከፍተኛ የመንግስት አመራር አባላት ጋር ገንቢ ውይይት በማካሄድ መንግስት በአጋርነት መንፈስ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት ጋር እንዲገናኙ ከማድረጉም በላይ በህግ ጥላ ስር ያሉትን ሳይቀር ማስጎብኘቱ ይታወሳል፡፡    

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ