አርዕስተ ዜና

ሦስት ሚሊዮን ብር የመንግስት ገንዘብ አክስረዋል የተባሉ ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ

21 Apr 2017
402 times

አርባምንጭ ሚያዝያ13/2009 ከአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ህንጻ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሶስት ሚሊዮን ብር የመንግስት ገንዘብ አክስረዋል ተብለው የተከሰሱ ሶስት ግለሰቦች እስከ ሰባት ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ፡፡

ግለሰቦቹ የተቀጡት የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት ባስቻለው ችሎት ነው፡፡

የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ በላይ ሙኩሎ እንደገለጹት አንደኛ ተከሳሽ ዘሪሁን በየነ ሀሰተኛ የግንባታ መረጃ በማቅረብ ጨረታውን ከማሸነፉም በላይ ደረጃው የማይፈቅደውን ግንባታ ፈጽሟል፡፡

በተጨማሪም የህንጻዉ መስኮት ፣ የጣሪያዉ ጠርዝና ሌሎችንም ስራዎች  ከገባው  ውል  ውጪ ደረጃውን ባልጠበቁ  ዕቃዎች መገንባቱ ተደርሶበታል፡፡ 

ሁለተኛው ተከሳሽ ደረጀ ባዩና ሶስተኛው ተከሳሽ ጥላሁን ጣሰው ደግሞ  ከመንግስት ወገን የተመደቡ ተቆጣጣሪ መሃንዲሶች ሆነው ግለሰቡ ይሰራ የነበረውን ጥፋት አይተው ባለማስቆማቸው ተባባሪ  ሆነው  ተገኝተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሶስት ሚሊዮን ብር የመንግስት ገንዘብ አክስረዋል ተብለው ግልሰቦቹ የተመሰረተባቸውን ክስ እንዲከላከሉ እድሉ ቢሰጣቸውም  ድርጊቱን  አምነው በመቀበላቸው ቅጣቱ ተላልፎባቸዋል፡፡

ዳኛው እንዳመለከቱት የግለሰቦቹ ድርጊት ወንጀል መሆኑን በሰነድና በሰው ማስረጃ ተረጋግጦባቸው፤ አንደኛው ተከሳሽ በሰባት ዓመት ጽኑ እስራትና 5 ሺህ ብር ፣ ሁለተኛውና ሶስተኛው ተከሳሾች ደግሞ  እያንዳንዳቸው  በአራት  ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተወስኗል ፡፡

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታዴዎስ ጨመሰ በሰጡት አሰተያየት በግለሰቦች ላይ የተላለፈው ቅጣት ሌላውን የሚያስተመር ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ህንጻውን ለመገንባት የወሰደው የመጀመሪያው ኮንትራክተር በፍጥነት መገንባት ባለመቻሉ ውሉ ተቋርጦ ከአንደኛው ተከሳሽ ጋር 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ውል የተገባ ቢሆንም የሚመለከተው  ክፍል ተገቢውን ቁጥጥር ባለማድረጉ ኪሳራ መድረሱን  ገልጸዋል ፡፡

ህንጻውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 10 ዓመታት የፈጀ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ