አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ምክር ቤቱ የኮሚሽኑን ምርመራ ውጤትና ምክረ ሀሳብ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ Featured

20 Apr 2017
661 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 12/2009 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ አስመልክቶ ይፋ ያደረገውን የምርመራ ውጤትና ምክረ ሀሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ ያጸደቀው ሪፖርት በሁከቱና ብጥብጡ ወቅት የተሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቶቷል ።

በሁከቱና በብጥብጡ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን የፌዴራልና የክልሎቹ መንግስታት በቅንጅት የማቋቋም ሥራ እንዲሰሩም ምክር ቤቱ በውሳኔው አካቷል።

የምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ዙሪያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማክሰኞ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርብ መመራቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት መሰረት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎችና በጌዲኦ ዞን በተካሄዱት ሁከትና ብጥብጦች የ669 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ ወደ 20 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል።

የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ዋነኛ መንስኤ ስር የሰደደውን የመልካም አስተዳደር ችግር በወቅቱ አለመፍታትና ለወጣቱ በቂ የሥራ እድል አለመፍጠር መሆኑም ተመልክቷል።

ሁከትና ብጥብጡን ያባባሱት መንግስትን በኃይል የመቀየር ዓላማ ያላቸው ሽብርተኛ የተባሉ ድርጅቶችና በህጋዊነት የተመዘገቡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ኮሚሽኑ የችግሩን መንስኤና ያስከተለውን ጉዳት የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ፣ ሚዛናዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ ያጣራውን ሪፖርትና ምክረ ሀሳብ ትክክለኛነት ቋሚ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል።

በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው "በሁከቱና በብጥብጡ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችና ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ" ሲል ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።

በሁከቱና በብጥብጡ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን የፌደራልና የክልሎቹ መንግስታት በቅንጅት ወደ ቀድሞ ኑሯቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን የማቋቋም ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉም በውሳኔው ተካቷል።

በባህር ዳር ከተማ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ አቅርበው በዕለቱ በቦታው ባለመገኘት ከተማዋን ለቀው የሄዱ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ላደረጉት ኃላፊነት ለጎደለው ተግባርና ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑም ምክር ቤቱ ወስኗል።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላትና ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ የወሰዱ የፀጥታ ኃይሎች ተገቢውን ማጣሪያ ተደርጎ ለህግ እንዲቀርቡ በኮሚሽኑ የቀረበውን ምክረ ሀሳብም ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ደግፎታል።፡

ምርመራቸው ተጀምሮ ያልተጨረሱ ሥራዎች በኮሚሽኑ ክትትልና ቁጥጥር ሂደት እየተጣሩ ፍጻሜ እንዲያገኙም ምክር ቤቱ ወስኗል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ሁከትና ብጥብጥ በተከሰተባቸው ቦታዎች  በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖርና አለመኖሩን መርምሮ ሪፖርት ማቅረብ ችሏል።

ይህ የኮሚሽኑ ተግባር በአገሪቷ እየተገነባ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓትና በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መርሆች በጥልቀት እንዲተገበሩ ያስችላል።

በተጓዳኝም በህግ አውጪው፣ በህግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው መካከል የክትትልና የቁጥጥር ስርዓቱ ጠንካራ እንዲሆን  እንደሚያደርግ አመልክተው፤ ይህም ተመሳሳይ ችግሮች ሲያጋጥሙ መንግስትና ህዝብ በመተባበር በራስ ዓቅም ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ነው የገለጹት።

በዚህም ምክር ቤቱ በኮሚሽኑ በቀረበው ሪፖርት መሠረት የመከታተል፣ የመደገፍ፣ እርምት የማስወሰድና በእርምት የማይመለሱት ላይ እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል።

ቀደም ሲል በኦሮሚያ 15 ዞኖችና 91 ወረዳዎች፣ በአማራ 5 ዞኖችና 55 ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን አራት ወረዳዎች ሁከትና ብጥብጥ  መከሰቱ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ምርምራውን ያካሄደው በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን፣ አባገዳዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችንና የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በማናገር መሆኑም ተገልጿል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ