አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር ለአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት በዓርአያነት የሚወሰድ ነው Featured

20 Mar 2017
854 times

አዲስ አበባ   መጋቢት  11/2009  የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር ለአፍሪካ-ቻይና ግንኙነት በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑን የቻይና ፕሬዚዳንት የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ዬቺ ገለፁ።

በአማካሪው ያንግ ዬቺ የተመራው የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሁለትዮሽ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

ያንግ ዬቺ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር ለቻይና-አፍሪካ ግንኙነት መጠናከር በአርአያነት የሚወሰድ ነው።

በአሁኑ ወቅት “ኢትዮጵያ በፈጣን ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት አፍሪካን እየመራች ነው” ያሉት ያንግ ዬቺ "ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አለን" ብለዋል።

ያንግ ዬቺ እንዳሉት ቻይና እያደገ ለመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የምታደርገውን ድጋፍና ትብብር ታጠናክራለች።

በተለያዩ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ ጋር ስትሰራ መቆየቷንና በተለይም በባቡርና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የምታደርገውን ድጋፍ ይበልጥ እንደምታጠናክር ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ለማሳካት የቻይና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ቻይና በኢትዮጵያ የልማት ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላት ገልፀው ድጋፏን እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የቻይና ድጋፍ እየተስፋፋ ባለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የአገሪቷ ባለሀብቶችም በተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በስፋት እየተሰማሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቻይና ፕሬዚዳንት የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ዬቺ በተመሳሳይ ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር ባካሄዱት ውይይት አገራቸው የአፍሪካ ግንኙነቷን በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማስተሳሰር ድጋፏን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

በአፍሪካ አገራትና ህዝቦች መካከል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውህደትን ለማጠናከር እንደምትሰራም ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ቻይና ለኢትዮጵያ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ እንድታጠናክር ጠይቀዋል።

ያንግ ዬቺ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ጋር ሁለቱ አገራት በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የሚያደርጉት ትብብር በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ተለዋጭ አባል በሆነችበት የፀጥታው ምክር ቤት በጋራ እንደሚሰሩ ተነጋግረዋል።

በመጪው ግንቦት ቻይና በምታካሄደውና ከ60 በላይ አገራት በሚሳተፉበት ዋን ቤልትና ሮድ ፎረም ኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎ በምታደርግበት ሁኔታ ዙሪያም ተወያይተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ