አርዕስተ ዜና

በልማት ሥራዎች ሴቶች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት ሰላምን ማስቀጠል ይገባል....የመቀሌ ከተማ ሴቶች

411 times

መቀሌ መጋቢት 5/2010 በሀገሪቱ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ሴቶችን በዘላቂነት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡ የመቀሌ ከተማ ሴቶች ገለጹ።

አዲሱ ትውልድ ለሰላም መጠናከር ዘብ እንዲቆም የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑም ተመልክቷል።

በየዓመቱ የሚከበረውን የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ ሴቶች እንዳሉት፣ በሰላምና ሰላም በሚታጣበት ወቅት ይበልጥ ተጠቃሚና ተጎጂ ሴቶች ራሳቸው ናቸው።  

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በመቀሌ ከተማ የሚኖሩት ታጋይ ወርቅነሽ በሽር እንዳሉት፣ በሀገሪቱ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ብቻ ሳይሆን ሀገርና ህዝብን ጠብቆ ለማቆየትም ሰላም የጎላ ፋይዳ አለው።

ሰርቶ መለወጥ፣ ያሰቡትን ማሳካትና ከልማቱም ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በተለይ ሴቶች በግንባር ቀደምነት ተዋናይ ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ላለፉት ዓመታት በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ሰላምና ልማት በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን በመገንዘብ በተለይ እናቶች ልጆቻቸውንና ወጣቱን ትውልድ ስለሰላም ዋጋ ማስተማር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሰላም ዋጋ በቀላሉ መታየት የለበትም ያሉት ታጋይ  እሰይነሽ  ኪሮስ በበኩላቸው፣ ሰርቶ መግባትም ሆነ ሀብት ማፍራት የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተዋል።

ሰላማቸው ከደፈረሰ የተለያዩ ሀገራት እርስ በርስ ከመጋጨትና ልማትን ከማጥፋት ውጪ የሚቀሰም መልካም ነገር እንደሌለ የገለጹት ታጋይ እሰይነሽ፣ ሰርቶ ለመለወጥና የወለዱት ለመሳምም ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶች የሰላም እጦት በሀገርና በዜጎች ላይ በተለይ በሴቶች ላይ የሚያስከትላቸውን የተለያዩ ችግሮች ለልጆቻቸው በማስረዳት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

 “ እናት ስለሰላም ማስተማር ከቤቷ ነው መጀመር ያለባት። በትጥቅ ትግል ወቅት በሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥና የዜጎች መብት እንዲከበር ልጇን ለትግል በክብር የሸኘች ናት። አሁንም ወጣቱ ትውልድ ወጥቶ ለመግባትና ሰርቶ ለማደር የሰላምን አስፈላጊነት ተረድቶ ሰላሙን ጠብቆ እንዲቆይ ሁሌም ልታስተምር ይገባል።’’

ከሃገር መከላከያ ሠራዊት በጡረታ መሰናበታቸውን የሚናገሩት ሻለቃ ደስታ ወረደ በበኩላቸው፣  በሀገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ በተደረገ የትጥቅ ትግል የወጣትነት ጊዜያቸውን በጦርነት አውድማ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ትውልድ በተለይ ሴቶች በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሰላምን ዋጋ በአግባቡ በመረዳት ለሰላማቸው በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

“ቤተሰብ የሀገር መሰረት፤ እናትም ደግሞ ዋነኛ የቤተሰብ ምሰሶ ናት” ያሉት ሻለቃ ደስታ፣ እናቶች ልጆቻቸው የሰላም አስፈላጊነትን እንዲረዱ ሁሌም የማስተማር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በወይይት መደረኩ ላይ የተገኙት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ ሴቶች በሀገሪቱ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የጎላ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ወደኋላ እንዳይመለስ አሁንም ግንባርቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።     

"በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተረጋገጠውን የሴቶችን እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት የአገርን ሰላም ዘላቂ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል ወይዘሮ ሮማን።

ለእዚህም ወጣቱ ትውልድ የሰላምን አስፈላጊነት ተገንዝቦ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ በኩል ከሴቶች በፊት ሊቀድም የሚችል ሌላ ኃይል አለመኖሩን ተናግረዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን