አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በየትኛውም አካባቢ ዜጎችን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅ ተግባር ላይ ትኩረት ይሰጣል Featured

18 Mar 2017
635 times

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 መንግስት ለአደጋ በተጋለጡ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎችን አስቀድሞ ከጉዳት የመከላከልና የመጠበቅ ስራዎች ለማከናወን ትኩረት እንደሚሰጥ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ዛሬ ሰጥተዋል።

ሰሞኑን በቆሼ አካባቢ የደረሰው አደጋ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አስቀድሞ ለማንሳት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ያመላከተ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በወንዝ ዳርቻዎችና "ይናዳሉ" ተብሎ በሚታሰቡ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች ችግር ሳይደርስባቸው፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሳይከሰት  ከወዲሁ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወን ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት በቆሼ አካባቢ  አደጋው ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊ የሆኑ የምግብ፣ የውሃ ፣ የብርድ ልብስና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ መሆናቸውንም አውስተዋል።

በቆሼ የተነሳውን አደጋ መንስኤ ለማወቅም ከቴክሳስ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተውጣጣ ቡድን ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ሌላው ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ያብራሩት፤ ሰሞኑን ከደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳዎች ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ አንዳንድ አካባቢ ገብተው በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ያስከተሉትን ታጣቂዎች በተመለከተ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ "መንግስት ኃይል መጠቀመን አልመረጠም" ያሉት ዶክተር ነገሪ፤ የሰው ሕይወት እንዳያልፍና የተወሰዱ ሕፃናትም በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

መንግስት አካባቢውን በማልማት፣ የመሰረተ ልማቶችን በመዘርጋትና ዜጎችን በመንደር ምስረታ በማሰባሰብ በየወቅቱ የሚነሱ ግጭቶች እንዲቆሙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እነዚሁ ታጣቂዎች የደቡብ ሱዳን መንግስትን እንደማይወክሉ የገለጹት ዶክተር ነገሪ፤ እስካሁንም ስድስት ሕፃናትና 185 ከብቶችን ለማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይም አደጋ ለመጣል የሞከሩ አካላትን አስመልክቶም ''እነዚህ አካላት እትብታቸው ኤርትራና አስመራ የሆነ የሚመራቸውም የኤርትራ መንግስት ነው ''ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት "ከየትኛውም ኃይል ይነሳል" ተብሎ የሚታስብ ስጋት እንደሌለ አመልክተው፤ እንደ አገር ግን ሉዓላዊነቷን ለማስከበር መከላከያ ሠራዊቷ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ብቃት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ