አርዕስተ ዜና

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል…ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ Featured

18 Mar 2017
599 times

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2009 የፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማድረስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያካሂዱ የቆዩት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ሸኝተዋቸዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲጠናከር ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በግላቸው ላበረከቱት አስተዋጽዖም የኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋና አቅርቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማድረስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ዘመናትን የዘለቀው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አሁን ላይ መድረሱ ጥንካሬውን እንደሚያሳይና ይህም በተለያዩ ዘርፎች ላይ መሰረት ማድረጉን ነው የጠቆሙት።

"በክፉ ጊዜም በደግ ጊዜም በጋራ የምንቆም አገር ነን፤ የሕዝብ ጥቅም ያስተሳሰረን መንግሥታት ሕዝቦች ነን" በማለት ያለውን አጋርነት ገልጸዋል።

ግንኙነቱ ያለምንም እንከን እዚህ ላይ ለመድረሱ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ አበርክቷቸው ትልቅ በመሆኑ ምሥጋና እንደሚገባቸው ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

"ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ምርት በጅቡቲ ወደብ የሚሄድ ነው" ይህም አጋርነታችንን ወሳኝ ያደርገዋል ብለዋል።

በቀጣይም በአገራቱ መካከል ቀሪ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አጋርነቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ቀንድ አገራትም ያላትን የግንኙነት አድማስ መልሳ በመመልከት ግንኙነቱን ለማንሰራራት ትሰራለችም ነው ያሉት።

በዚህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ውህደትና ለዓለም ትስስር የበኩሏን ለመወጣት ጥረት እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለሁለቱ ምክር ቤት አባላቶች አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነት ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋርም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ሁለንተናዊ ትስስር ይበልጥ ሊጠናከርበት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር በመሆን ለጅቡቲ አምባሳደሮች መኖሪያ የሚሆን የግንባታ መሰረት-ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማስመዝገብ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ ሥር ሆነው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ