አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የፖለቲካ ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ ህዳሴ በሚል የተዘጋጀው መጽሀፍ ተመረቀ

18 Mar 2017
1097 times

አዲስ አበባ 9/2009 የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ዓለምነው መኮንን 'የፖለቲካ ኢኮኖሚና የኢትዮጵያ ህዳሴ' በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሀፍ ዛሬ ተመረቀ።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ሌሎች ከፌደራል፣ ከአዲስ አበባና ከክልል የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

አቶ ዓለምነው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የመጽሃፉ ዓላማ በየጊዜው ለሚከሰቱ የአስተሳሰብ ችግሮችን እልባት ለማበጀት በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ማመላከት ነው።

መጽሀፉ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸው ወደ ብልጽግና እንዲያመሩ የተከተሉትን መንገድ በተሞክሮነት ቀምሮ የያዘ መሆኑን አስረድተዋል። 

''የመጽሀፉ ዓላማ ንድፈ-ሀሳብና ተግባራዊ ተሞክሮን ባገናዘበና ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ስኬትም ሆነ ውድቀት የተጠናወተው የፖቲካ ኢኮኖሚ ምንነትና አዝጋሚ ለውጦችን በንጽጽር ለማሳየት መሞከር ነው'' ብለዋል።

መጽሀፉ የበለጸጉ አገራት የተከተሉትን የዴሞክራሲ ሂደትና ያገኙትን ውጤት በተብራራ መልኩ እንደሚያስቀምጥም ነው የተናገሩት። 

በአገሮች ላይ የታዩ መዋቅራዊ ለውጦች፣ ውጤቶቻቸውና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ውጤታማነት በቅደም ተከተል መቅረቡንም እንዲሁ።

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምንነት፣ ያለፈባቸው አዝጋሚ ሂደቶች፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት አማራጭ አስተሳሰቦች፣ የሊበራል፣ የሶሻልና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ባህሪያት ልዩነት መጽሃፉ ያካተታቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ፖሊሲ አውጪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች መጽሀፉን አንደ ማጣቀሻ መጠቀም እንደሚችሉ ነው አቶ ዓለምነው የተናገሩት።

መጽሀፉ ለህትመት እንዲበቃ የብአዴን አመራሮችና ምሁራን አስተያየት በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የመጽሀፉ ለንባብ መብቃት የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ በጠራ አስተሳሰብ ለመምራት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

''በተጣበበ ጊዜ ይህን መሰል ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያለው መጽሀፍ ለንባብ ማብቃት ሊበረታታ ይገባል'' ያሉት አቶ ደመቀ ሌሎች አመራሮችም ተግባሩን በአርአያነት በመውሰድ ለሀሳብ ትግሉ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብለዋል።    

አቶ ዓለምነው ከትግሉ ጀምሮ የላቀ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን አስታውሰው ''ከጸሀፊው ጊዜን ከቤተሰብና ከራስ መደበኛ ስራ ጋር  አመጣጥኖ መሄድ እንደሚቻል መማር ይኖርብናል ነው ያሉት።

በአገሪቱ የተጀመረውን የህዳሴ መስመር የተቃና ለማድረግ አማራጭ አስተሳሰቦች ለህዝቡ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

''እየተለወጠ ባለው ዓለም ከጊዜው ጋር የሚራመድ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አመራር ያስፈልጋል'' ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ አቶ ዓለምነው አንድ እርምጃ ተጉዘዋል ሌሎች አመራሮችም የሳቸውን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

መጽሀፉ በውስጡ የያዛቸው ጉዳዮችን ወደ ህዝብ ተደራሽ ለማድረግና የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው መጽሀፉ ለንባብ ባህል መዳበር ተጨማሪ ግብአት ይሆናል ብለዋል።

''አሁን ላለውና ለቀጣይ ትውልድ በሳል የአዕምሮ ውጤታቸውን፣ ዕውቀታቸውና የካበተ ልምዳቸውን በጽሁፉ ማስቀመጥ በመቻላቸው ሊመሰገኑ ይገባል ነው'' ያሉት።

መጽሀፉ ዜጎች የአገራቸውን ወደፊት የልማት አቅጣጫዎች እንዲመዝኑ በማድረግ የሚስተዋሉ የዕውቀት ክፍተቶችን የሚሞላ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።  

አምባሳደር ገነት ዘውዴ ''ሌላ ስጦታ ይረሳል የመጽሀፍ ስጦታ ግን ሁሌም አይዘነጋም'' ሲሉ ነው ያመሰገኑት።

''አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚፈለገው ደረጃ ህዝቡ ውስጥ ግንዛቤው ሰርጿል ማለት ይቻላል'' ያሉት አምባሳደሯ መጽሀፉ በዚህ በኩል የሚስተዋልን ክፍተት ለመሙላት አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

መጽሀፉ 405 ገጾች ያሉት ሲሆን በአራት ምዕራፍና በ10 ክፍሎች የተዋቀረ ነው።

የመጀመሪያው የመጽሀፉ የምረቃ ስነ-ስርዓት በባህርዳር ተካሂዷል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ