አርዕስተ ዜና

በአማራ ክልል የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅሙ ያዋለው ግለሰብ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

454 times

ባህርዳር መጋቢት 4/2010 የህዝብና የመንግስት ገንዘብ ለግል ጥቅሙ አውሎ ያገኘውን ግለሰብ በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ማድረጉን የአማራ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገፁት ተከሳሽ አዳነ እንየው የቅጣት ውሳኔው የተላለፈበት በፈፀመው ከባድ የዕምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

ተከሳሹ ከጥር 1/2003 እስከ መስከረም 30/2009 በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ዋና ገንዘብ ያዥ ሆኖ ሲሰራ በፈፀመው ከባድ የሙስና ወንጀል ኮሚሽኑ ክስ መስርቶበታል።

"በወቅቱም ተከሳሹ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከሁለት ሚሊዮን 977 ሺህ ብር በላይ አጉድሎ መገኘቱ በተደረገ የኦዲት ሪፖርት ምርመራ ተረጋግጧል" ብለዋል።

የኮሚሽኑ ዓቃቢ ህግም በግለሰቡ ላይ ከጥር ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ክስ በመመስረት ባደረገው ክርክር የደቡብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሹን ጥፋተኛነት አረጋግጧል።

"ተከሳሹ በአቃቢ ህግ የቀረበበትን ክስ በማስረጃ መከላከል ባለመቻሉም ፍርድ ቤቱ መጋቢት 3/2010 በዋለው ችሎት በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በአምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኖበታል" ብለዋል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን