አርዕስተ ዜና

የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፉ የመረጃ ቅብብሎሽ አለመጠናከር አገሪቷን ዋጋ እያስከፈላት ነው

415 times

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2010 የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የመረጃ ቅብብሎሽ የተጠናከረ አለመሆን አገሪቷን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተናገሩ።

የሁሉም ክልሎችና የፌዴራል ተቋማት የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የጋራ ግምገማ ፎረም በመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የተሳተፉ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰሩት ስራ የተጠናከረ ባለመሆኑ ህዝቡ በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች እየተደናገረ መሆኑን አምነዋል።

በዚህም ምክንያት ወጣቱ አፍራሽ ዓላማ ይዘው ለሚንቀሳቀሱ አካላት አጀንዳ ሰላባ እየሆነ አገሪቷን ለሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም እየዳረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

ትክክለኛው የህዝብ ጥያቄ ምላሽ በአግባቡ እንዳይመለስና ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ እያደረገ ነውም ብለዋል ባለሙያዎቹ።

የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተሾመ ''በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የታየውን  ደካማ አፈጻጸም በደንብ አስቀምጠን መሄድ አለብን  ፤ ለወደፊቱ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉም መቀመጥ መቻል አለባቸው''ነው ያሉት

''በአንዳንድ አካባቢዎች በህዝብ መፈናቀልም ሆነ ሌሎች የተስተዋሉ ችግ ሮች የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ስራችን ደካማ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፤ ከዚህ ተምረን ቀጣይ እንዴትና ምን በመስራት ውጤታማ መሆን እንችላለን  የሚለው መሰመር ያለበት ጉዳይ ነው'' ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ናቸው፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው በመንግስት በኩል ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦና ተነጋግሮ ችግሩን ለመፍታት ዝግጁነት መኖሩን ገልጸዋል።

ይህን ህዝቡ እንዲገነዘብ ማድረግና ህዝቡም አቅጣጫዎችን ተረድቶ ተሳታፊ እንዲሆን የማድረግ የተግባቦት ስራ ላይ ግን ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

በማህበራዊ ሚዲያው ሌላ ዓላማ የሚያራምዱ አካላትም ይህን ክፍተት እየተጠቀሙ ህዝቡን እያደናገሩት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ትክክለኛ መረጃዎችን በአግባቡና በፍጥነት ለህዝቡ ማድረስ ላይ ሁሉም ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፤ የህብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ መሆኑንም አውስተዋል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን