አርዕስተ ዜና

በክልሉ ከተሞች መሬት አስተዳደርና ልማት ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን እንደሚገባ ተመለከተ

414 times

አክሱም መጋቢት 4/2010 በትግራይ ክልል ከተሞች መሬት አስተዳደርና ልማት ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ማስፈን እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በክልሉ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በከተማ መሬት አስተዳደርና ልማት  አፈጻጸም ላይ በየደረጃው ለሚገኙ የህዝብ ተመራጮች ስለሚኖራቸው ድርሻ  ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያዘጋጀው ስልጠና በአክሱም ከተማ ተካሂዷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዕጻይ እምባየ  በየደረጃው የሚገኙ  የምክር ቤት አባላት የክትትልና ቁጥጥር ስርዓት ማጎልበት ላይ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ፈጻሚ አካል ባወጣው እቅድ መሰረት የመገምገም፣ የመከታተልና ተጠያቂ ማድረግ  የህዝብ ተመራጮች ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ህገ ወጥ ግንባታ እና የይዞታ ማረጋገጫ ችግር እየተስተዋለ ያለው  የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚው አካል መከታተል እና መቆጣጠር ባለመቻሉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም  የከተማ ልማት፣የመሬት ምዝገባና መረጃ አያያዝ ስርዓት የሚታየውን የአሰራር ክፍተት ለማስተካከል በየደረጃው የሚገኙ ምክር  ቤቶች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በመሬት አስተዳደርና ልማት ላይ የወጣውን አዋጅ፣ደንቡና አሰራርን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አካሄድን በመከተል መፈጸም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

"በነባር ይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ፣በህገ ወጥ ግንባታዎች፣ህገ ወጥ ይዞታና በካሳ አከፋፈል የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱ ይበልጥ ለማጠናከር ቋሚ ኮሚቴው ይሰራል "ብለዋል፡፡

በመቐለ ከተማ  የሓድነት ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል  ወይዘሮ ኤልሳ ኪዳነማርያም እንዳሉት በመሬት አስተዳደር ፈፃሚ አካል የወጣውን አዋጅና መመሪያ በመከታተል በኩል ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በከተማ የመሬት ላይ የሚታዩ  ችግሮች  ለመፍታት ያልተቻለው ፈጻሚ አካላት እና የምክር ቤት አባላት የተሰጣቸው ኃላፊነት ባለመወጣታቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የነባር  ባለይዞታ ማረጋገጫ፣ህገ ወጥ ግንባታና የካሳ አከፋፈል ላይ የሚስተዋሉት ክፍተቶች  የመልካም አስተዳደር ችግር መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአድዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል አቶ ገብረእግዚአብሔር አስመላሽ  ናቸው፡፡

በስልጠናው ያገኙት እውቀት ተጠቅመው የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፈን ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ለሶሰት ቀናት በተዘጋጀው ስልጠና ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የህዝብ ተመራጮች ተሳትፈዋል፡፡

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን