አርዕስተ ዜና

አዋጁ ሰላምን ለማረጋገጥ አስተዋፆው የላቀ ነው - የአክሱም ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

401 times

አክሱም መጋቢት 4/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝብና የሃገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን በአክሱም ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ ።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር  አጽብሃ ተክለ በሰጡት አሰተያየት አዋጁ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከትና አለመረጋጋት በማስቆም የቀድሞው ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ አስተዋጽኦ አድርጓል ።

ሁከቱን ተከትሎ ተስተጓጉሎ የነበረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴም ወደ ነበረበት እንዲመለስ  ማድረጉን ተናግረዋል ።

"ይሁንና አዋጁ ብቻውን በቂ አይደለም" ያሉት መምህር አጽብሃ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ባለቤት ከሆነው ህዝብና መንግስት ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

"በተለይ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ከባድ የቤት ስራ አለባቸው" ብለዋል ።

እንደ መምህር አጽብሃ  ገለፃ የመንግስት አካላት ከፖሊቲካ ተፎካካሪዎች፣ ከምሁራን፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከመላው ህብረተሰብ ጋር ተከታታይ የሰላም መድረክ በማዘጋጀት ፈጣን መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ።

"አዋጁ ከቦታ ወደ ቦታ ያለስጋት ተንቀሳቅሰን እንድንሰራ ዋስትና ሰጥቶናል " ያሉት ደግሞ በከተማው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ዮሃንስ ገብረመድህን ናቸው።

በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር የትራንስፖርት አገልግሎት በመስተጓጎሉ ከአዲስ አበባ እቃዎችን ወደሚኖሩበት ከተማ ለማምጣት ተቸግረው እንደቆዩ አስታውሰዋል ።

"ሁኔታው በንግድ ስራየ ላይ ጉዳት አድርሶብኝ ነበር"ያሉት አቶ ዮሃንስ ሰርቶ ለመለወጥ ሰላም መሰረት በመሆኑ የአዋጁን መውጣት እንደሚደግፉ ተናግረዋል ።

የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከህዝብ የሚጠበቀውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል ።

በከተማው የ‘‘ክንደያ ቀበሌ‘‘ ነዋሪ ወይዘሮ ህይወት መለስ በበኩላቸው "አዋጁ የሃገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት በመመለሱ  እኔም ከስጋት ተላቅቂያለሁ" ብለዋል ።

"በሁከትና ግርግር ዋና ተጠቂ ሴቶችና ህጻናት ናቸው" ያሉት ወይዘሮ ህይወት አዋጁ የሃገሪቱን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ።

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል የ3ኛ አመት ተማሪ ዲደዲያ ተስፋሁን በበኩሉ በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሶ ከአዋጁ በኋላ ስጋቱ ሙሉ ለሙሉ መወገዱን ተናግሯል ።

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን