አርዕስተ ዜና

በአገሪቱ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል - ምሁራን

17 Feb 2017
359 times

መቀሌ የካቲት 10/2009 ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት የአገሪቱ ልማት ለማፋጠን የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በትግራይ ክልል የሚገኙ ሦስት ምሁራን ገለጹ።

የህወሓት  42ኛ ዓመት የምስራታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ምሁራኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየተ የካቲት 11 ቀን የተለኮሰው የትጥቅ ትግል በድል ከተጠናቀቀ ማግስት ጀምሮ በአገሪቱ ሰፊ የከፍተኛ ትምህርት እድል ተከፍቷል፡፡

ይህም ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሄድ በልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ምሁራኑ ገልፀዋል፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ ተማራማሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ሃይለ እንዳሉት፣ ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ በተፈጠረው ሰፊ የትምህርት እድል በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማካሄድ መንገድ ከፍቶላቸዋል።

ከድል ማግስት ጀምሮ ከተከፈቱት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲም ከተለያዩ የዓለም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር አቅሙን ከማሳደግ ባሻገር ምሁራን የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲያካሂዱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

አሳቸውም ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እስካሁን ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ከ96 የሚበልጡ የጥናትና ምርምር ስራዎች ማከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችም ከ300 ላይ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማቅረብ ኢትዮጰያን ያላትን በጎ ገጽታ ለማስተዋወቅ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ያካሄዱዋቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች አብዛኛዎቹ በትግራይ ክልል የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነት ለማረጋገጥ እያስቻሉ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አስረድቷል።

በቀጣይም የጥናትና ምርምር ስራውን አጠናክረው ከመቀጠል ባሻገር ወጣት ተመራማሪዎችን በማፍራትና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስቀጠል የሰማእታትን አደራ ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንትና ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፈቴን አባይ በበኩላቸው፣ ''ከዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ እስከ ፕሮፌሰር የደረሱት የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ባካሄዱት መራራ ትግልና በከፈሉት የህይወት መስዋእትነት ነው'' ብለዋል።

በደርግ ስርዓት የከፍተኛ ትምህርት ቀርቶ የተገደሉባቸውን ቤተሰቦች ለመቅበር እንኳን ዕድሉ እንደተነፈጋቸው ያስታወሱት ፕሮፌሰሯ፣ ከስርዓቱ መገርሰስ በኋላ በተስፋፋው የትምህርት እድል እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ምሁራን ለአገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ በር መክፈቱን ተናግረዋል፡፡

እርሳቸውም በግብርናና ገጠር ልማት ዘርፍ የተሻሻሉ ምርጥ ዝርያዎች በምርምር በማውጣት ለምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታትም ከ65 በላይ የምርምር ስራዎችና 200 የሚሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የራያ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ምሁራንም በሰማእታት የተገኘውን ሰላም፣ልማትና ዲሞክራሲ በማስቀጠል ለሃገራቸው እድገት እንዲተጉ ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

ከደርግ ውድቀት በፊት ጥቂት የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ባለፉት 26 ዓመታት በተደረገ ጥረት በግንባታ ላይ ያሉትን ጨምሮ 40 ያህል መድረሳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ