አርዕስተ ዜና

የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ የህዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ ትግሉን በፅናት እንደሚቀጥሉ ህወሓት አስታወቀ Featured

16 Feb 2017
1063 times

መቀሌ የካቲት 9/2009 የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦች ጋር በመሆን የህዳሴውን ጉዞ እውን ለማድረግ ትግሉን በፅናት እንደሚቀጥሉ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 42ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ማዕከላዊ ኮሚቴው  ለኢዜአ በላከው መግለጫ የ42 ዓመታት የትግል  ጉዞ ምንጭ በየመድረኩ እየጠራና እየፋፋ መምጣቱን ገልጿል፡፡

በመግለጫ ላይ እንደተመለከተው  የውስጥና የውጭ ጠላቶች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱና የህዳሴ ጉዞውን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት አይሳካላቸውም፡፡

የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት በጋራ በመሆን የህዳሴ ጉዟችን ለማሳካት ዳግም ቃል እንገባለን  ሲል ድርጅቱ በመግለጫው ላይ  አመልክቷል፡፡

ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ለ17 ዓመታት ያካሄዱት መራራ የትጥቅ ትግል የሀገሪቱ ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲመሰርቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጿል፡፡

"በዚህም በድህነት የዓለም ተምሳሌት ተደርጋ ትታይ የነበረችው አገራችን አሁን ፈጣን ፣ፍትሃዊ  ልማትና ሰፊ መሰረት ያለው ዲሞክራሲ ለመገንባት  ርብርብ ላይ ነን " ብሏል ህወሓት በመግለጫው፡፡

ህወሓት በሰፊ ህዝባዊ መሰረት የጸና ፣  በሳይንሳዊና ስነ ሀሳባዊ የበለፀገ ፖለቲካዊ ብቃቱን ያስመሰከረ መሪ ድርጅት መሆኑ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡ 

በየጊዜው የሚያጋጥሙትን   ፈተናዎች  በብቃት በመሻገር አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ  መጥቷል ብሏል፡፡

የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ጋር በመሆን የህዳሴውን  ጉዞ  እውን ለማድረግ ትግሉን  በፅናት እንደሚቀጥሉ  ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው  አስታውቋል፡፡

ህወሓት 42ኛ ዓመቱን ሲያከብር ያለፉት የ15 ዓመታት የህዳሴ ጉዞ በጥልቀት በገመገመበት  ማግስት መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ህወሓት  ካለፉት  ዓመታት የህዳሴ ጉዞ ልምድና ትምህርት በመውሰድ "አሁንም ድርጅታችን በጥልቀት በማደስ ለተልዕኮው ብቁ እናደርገዋለን" በሚል መሪ ሀሳብ በዓሉ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

በገጠርና በከተማ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች እንደትላንቱ ከመሪ ድርጅቱ ጎን በመሰለፍ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የፈጠራቸውን እድሎች በመጠቀም ኑሮውን ለማሻሻል እያደረጋቸው ባለው ጥረት ለውጥ እያስመዘገበ ነው፡፡

"አርሶ አደሩ ትላንት የማያውቀውን አሁን ሀብትና ጥሪት እያፈራ መሆኑ ማረጋገጫ ነው " ብሏል ህወሓት በመግለጫው፡፡

መስመሩ ለከተማው ነዋሪ ህዝብም የኑሮው መሻሻል  ዋስትና መሆኑንም በርካታ ማረጋገጫ እንዳሉትም ድርጅቱ አብራርቷል፡፡

ህወሓት ለትግራይ ህዝብ፣ለእህትና አጋር ድርጅቶች ፣ ለኢህአደግ አባላት፣ ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንኳን ለ42ኛ አመት የልደት በዓል አደረሳችሁ ብሏል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ