አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን ተጀመረ Featured

11 Jan 2017
679 times

ጅግጅጋ ጥር 3/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል 29 ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ በሰውና እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ 470 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ምግብና መኖ ማቅረብ መጀመሩን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን በጅግጅጋ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃሙድ ኡመር ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ እንደተናገሩት በክልሉ በተከሰተው ድርቅ አንድ ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጐች ለምግብ እህል እጥረት ተዳርገዋል፡፡

በድርቅ ለተጠቁ ዜጐች አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግ 470 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ለእንስሳት መኖ፣ ውሃና የምግብ እህል የማቅረብ ስራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥረት 100 ሺህ እስር የእንስሳት መኖ ለጋሻሞና ለሽላቦ ወረዳዎች እየተከፋፈለ ሲሆን ለሌሎች ወረዳዎችም  የማከፋፈሉ ስራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በድርቅ በተጠቁት ወረዳዎች የሚገኙ 270 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በቂ ባለሙያ ተመድቦና ነዳጅ ቀርቦላቸው የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የምግብ እህል ድጋፉም ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር እየተከፋፈለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በውሃ፣ በመንደር ማሰባሰብ፣ በትምህርት ፣ በገጠር መንገድ ግንባታና ገቢ ማሰባሰብ ዙሪያ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ርእሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ በመወያየት ላይ ነው፡፡

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የክልሉ ምክር ቤት አራተኛ መደበኛ ጉባኤ የ2009 ተጨማሪ በጀትና ሌሎች አዋጆችን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ